የብሪታንያ ዩንቨርስቲ በአስማት እና ጥንቆላ የማስተርስ ድግሪ ማስተማር ሊጀምር ነው
ትምህርቱን ለመማር የሚፈልጉ ሰዎች መብዛት ለትምህርት መጀመር ምክንያት ነው ተብሏል
የአስማት ድህረ ምረቃ ፕሮግራም ከአንድ ዓመት በኋላ እንደሚጀመር ተገልጿል
የብሪታንያ ዩንቨርስቲ በአስማት እና ጥንቆላ የማስተርስ ድግሪ ማስተማር ሊጀምር ነው።
የብሪታንያው ኤክስተር ዩንቨርስቲ የአስማት ትምህርትን በሁለተኛ ድግሪ ማስተማር ሊጀምር መሆኑን አስታውቋል።
በማህበራዊ ሳይንስ ጥናት ዘርፍ ታዋቂ የሆነው ይህ ዩንቨርሲቲ ጥንቆላ እና አስማት በህብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ታሪክ እና አስተዋጽኦ ለመዳሰስ ማቀዱንም አስታውቋል።
የአስማት ትምህርትን ለመማር የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ዩንቨርስቲው የትምህርት ክፍሉን ለመክፈት ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ ገልጿል።
የትምህርት ክፍሉ ስለ ጥንቆላ እና አስማት ታሪክ፣ ለሳይንስ እና ለዓለም ህዝብ ያላቸውን አበርክቶ በጥልቀት መዳሰስ ላይ እንደሚያተኩር በዩንቨርሲቲው መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ኤሚሊ ሴሎቭ ለጋርዲያን ተናግረዋል።
ይህ ትምህርት ክፍል ከዚህ በፊት እንዲሰጥ ታስቦ የነበረ ቢሆንም ትምህርቱ ቢሰጥ አሁን ላለው ዘመናዊ ትውልድ ላይጠቅም ይችላላ በሚል እንዲቀር ተደርጎ ነበር ተብሏል።
ይሁንና አስማት የሁልጊዜ የህይወታችን አካል በመሆኑ ትምህርቱ እንዲሰጥ መወሰኑን ፕሮፌሰር ኤሚሊ ተናግረዋል።
ሀይማኖት፣ ስነ ጽሁፍ፣ ሴታዊትነት፣ ባህል፣ የማህበረሰብ ጥናት እና ሌሎችም በዚህ ትምህርት ውስጥ የሚዳሰሱ ጉዳዮች ይሆናሉ ተብሏል።
በፈረንጆቹ 2022 ላይ በሀይማኖቶች ላይ በተሰራ ጥናት መሰረት ኢ-አማኝነት እና ሻማኒዝም (በሰሜን አውሮፓ ሀገራት ያለ ሀይማኖት ነው) የተሰኘው እምነት በፍጥነት እያደገ ያለ ሀይማኖት ሆኖ መገኘቱ ተገልጿል።
ዩንቨርሲቲው ከ100 በላይ ሰዎች ጥንቁልና እና አስማት መማር እንደሚፈልጉ ፍላጎታቸውን እንደገለጹለትም አስታውቋል።
በዚህ ዩንቨርስቲ ይሰጣል የተባለው ይህ የድህረ ምረቃ ትምህርት የምዕራባዊያን ባህላዊ ዘዴዎችን ከሌሎች አማራጮች ጋር ባቀናጀ መልኩ ይሰጣል ተብሏል።
ተማሪዎች ስራዎቻቸውን እና ሙያቸውን ሊያሳዩ የሚችሉባቸው ስፍራዎች ተለይተዋል የተባለ ሲሆን ህዝብ የሚዝናናባቸው ቦታዎች፣ ቅንጡ ስፍራዎች እና ሌሎችም ቦታዎች እንደሚዘጋጁ ተገልጿል።
ተማሪዎች የንድፈ ሀሳብ እና የተግባር ትምህርታቸውን መተግበር በሚችሉበት ሁኔታ ትምህርቱን እንደሚያገኙም ተገልጿል።