ሩሲያ ወደ ጀርመን የሚያልፉ የጋዝ ማስተላለፊያዎቿን መዝጋት ጀመረች
ሆኖም ጀርመን ሩሲያ ጋዝ ማስተላለፏን በዚያው ልታቆም ትችላለች በሚል ከፍተኛ ስጋት ላይ ወድቃለች
የጋዝ ማስተላለፊያዎቹ ለጥገና በሚል ነው የተዘጉት
ሩሲያ ጋዝ ወደ ጀርመን የምታስተላልፍበትን ዋና መስመር ኖርድ ስትሪም አንድን ዘጋች፡፡
የጋዝ መተላለፊያ መስመሩ የተዘጋው ልክ በየዓመቱ እንደሚደረገው ሁሉ ለዓመታዊ ጥገና ነው፡፡
ሆኖም ኖርድ ስትሪም 1 ለጥገና በሚል መዘጋቱ ለጀርመን አልተዋጠም፡፡
ሩሲያ የምታስተላልፈውን ነዳጅ በዚያው ለማቆም አስባ ሊሆን ይችላል በሚል ከፍተኛ ስጋት ላይ ወድቃለች፡፡
በተለይም ጋዝፕሮም የተሰኘው የመተላለፊያ መስመሮቹ አስተዳዳሪ የሩሲያ መንግስት የነዳጅ ኩባንያ ወደ ሲያስተላልፍ የነበውን ጋዝ በ60 በመቶ መቀነሱ ጀርመን ይበልጥ እንድትሰጋ ምክንያት ሆኗል፡፡
ሆኖም ጋዝፕሮም መተላለፊያው የተዘጋው ባጋጠሙ የቴክኒክ ብልሽቶች ምክንያት እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ይህ ግን ከቴክኒክ ችግሮች ይልቅ ጉዳዩ ፖለቲካዊ ነው ሲሉ ሩሲያን ለወቀሱ የጀርመን ፖለቲከኞች በፍጹም የሚዋጥ አይደለም፡፡ አለመረጋጋትንና የዋጋ ንረትን ለመፍጠር በማሰብ የተደረገ ተንኮል ነው በሚል ይከሳሉ፡፡
ጋዝፕሮም ግን ለጀርመን የኃይል አቅርቦት የልብ ትርታ ሆኖ በማገልገል ላይ ያለው ኖርድ ስትሪም 1 እስከ ፈረንጆቹ ሃምሌ 21 ድረስ ከአገልግሎት ውጭ ሆኖ እንደሚቆይም አስታውቋል እንደ ኤ.ፒ ዘገባ፡፡
ጀርመን በጋዝ አቅርቦቱ መቀነስ ምክንያት በቂ ኃይልን ሳታገኝ መቆየት እንደሚከብዳት የገለጸችው ካናዳ ወደ እርሷ ከሚተላለፈው የሩሲያ ነዳጅ የተወሰነውን ወደ ጀርመን ለማስተላለፍ ፍቃድ ሰጥታለች፡፡
ሩሲያ ልዩ ያለችውን ዘመቻ በዩክሬን መጀመሯን ወረራ ነው በሚል ያወገዙ ጀርመንን ጨምሮ አሜሪካና ምዕራባዊ አጋሮቿ ዘርፈ ብዙ ማዕቀቦችንና እገዳዎች በሞስኮው ላይ ጥለዋል፡፡ ከሩሲያ ነዳጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ ያስችለናል ያሏቸውን እርምጃዎች እንደሚወስዱ ሲዝቱም ነበረ፡፡ ሆኖም ጥገኝነቱ በቀላሉ ለመላቀቅ የሚቻል አይደለም፡፡
35 በመቶ ያህል የነዳጅ ፍጆታዋን ከሩሲያ የምታገኘው ጀርመን በተለይ ይህን ማድረጉ ከብዷታል፡፡ በግዝፈቱ ከአውሮፓ የሚጠቀሰው ምጣኔ ሃብቷ ችግር ላይ ሊወድቅ እንደሚችልም የሚያስጠነቅቁ በርክተዋል፡፡