ፕሬዝዳንት ፑቲን ለሁሉም የዩክሬን ዜጎች የሩሲያ ፓስፖርት እንዲሰጣቸው አወጁ
የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ አምስተኛ ወሩን ሊይዝ ጥቂት ቀናት ቀርተውታል
ሩሲያ ከዚህ በፊት ለዶምብአስና ሉሃንስክ ግዛት ነዋሪዎች የሩሲያ ፓስፖርትን ስትሰጥ ነበር
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለሁሉም የዩክሬን ዜጎች የሩሲያ ፓስፖርት እንዲሰጣቸው የሚያስችል አዋጅ ማውጣታቸው ተነግሯል።
ሞስኮ ከዚህ በፊት በሩሲያ ቁጥጥር ስር በዋሉ የዩክሬን ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ፓስፖርት ስትሰጥ የቆየች ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ለሁሉም የዩክሬን ዜጎች የሩሲያ ፓስፖርት እንዲሰጣቸው የፕሬዝዳንት ፑቲን መንግስት አውጇል ተብሏል፡፡
ታስ የተሰኘው የሀገሪቱ ዜና አገልግሎት እንዳስነበበው ከሆነ በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ፊርማ በወጣ አዋጅ ከዚህ በፊት በከፊከል ለዩክሬን ዜጎች ብቻ ይሰጥ የነበረው የሩሲያ ፓስፖርት ለሁሉም ዩክሬናዊያን ይሰጣል ተብሏል፡፡
ዩክሬን በበኩሏ “ሩሲያ እያደረገችው ያለው ተግባር በግዛቴ ውስጥ የሩሲያ ዜጎች መፍጠር ነው” በማለት ማውገዟ ተገልጿል።
ሩሲያ በዩክሬን ግዛት ውስጥ ፓስፖርት መስጠት መጀመሯ የዩክሬንን የግዛት እንደነት የሚፈታተን እና ዓለም አቀፍ ህጎችን የጣሰ መሆኑንም አስታውቃለች።
በቅርቡም የመጀመሪያው የሩሲያ ባንክ በሩብል መገበያየትና የሩሲያን የቴሌኮምና ሌሎችንም አገልግሎቶች መጠቀም በጀመረው የኬርሶን አካባቢ በቅርቡ ስራ እንደሚጀምር የአካባቢው የአስተዳደር አካላት ማስታወቃቸው ይታወሳል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዚህ በፊት በሰጡት መግለጫ የዘመናዊቷ ሩሲያ ዕጣ ፋንታ የሚወሰነው የቀድሞ ግዛቶቿን ማስመለስና ማጠናከር መሆኑን ማስታወቃቸውም አይዘነጋም፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ወይም ኖቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ይፋዊ ጦርነት ካመሩ አምስተኛ ወር ሊሞላቸው ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርቶታል፡፡
በዚህ ጦርነት ምክንያት ከ15 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የጠፈናቀሉ ሲሆን በመቶ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት ደግሞ መውደሙን ተመድ አስታውቋል፡፡