በጋዛው ጦርነት የሟቾች ቁጥር 18ሺ ገደማ ደረሰ
የሀውዊ ታጣቂዎች በቀይ ባህር በኩል በእስራኤል ላይ የሚሰነዝሩት ጥቃት ግጭቱን ወደ ቀጣናው ያስፋፋዋል የሚለውን ስጋት ጨምሯል
የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ከባለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ 97 የእስራኤል ወታደሮች ተገድለዋል
በጋዛው ጦርነት የሟቾች ቁጥር 18ሺ ገደማ ደረሰ
በእስራኤል እና ሀማስ ጦርት የሞቱ ፍልስጤማውያን ቁጥር 17ሺ700 መድረሱን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
አሜሪካ በተመድ የጸጥታው ምክርቤት የቀረበውን የተኩስ አቁም የውሳኔ ሀሳብ እንዳይጸድቅ ካደረገች ከአንድ ቀን በኋላ እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን የአየር ጥቃት እና የከባድ መሳሪያ ድብደባ አጠናክራ ቀጥላለች።
የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ከባለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ 97 የእስራኤል ወታደሮች ተገድለዋል።
ግጭቱ ወደ ቀጣናው ይስፋፋል የሚለው ስጋት ባየለበት በዚህ ወቅት የሀውቲ ታጣቂዎች ምግብ እና መድሃኒት ጋዛ እስከሚገባ ድረስ ማንኛውም መርከብ በቀይ ባህር እና በአረቢያን ባህር በኩል ወደ እስራኤል እንዳያልፍ እገዳ መጣላቸውን ገልጸዋል።
ታጣቃዎቹ እግዱን ተከትሎ ወደ እስራኤል በሚያቀና ማንኛውም መርከብ ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ አስጠንቅቀዋል።
የሆውቲ ባለስልጣናት ጥቃቱን የሚፈጽሙት ለፍልስጤማውያን ድጋፋቸውን ለማሳየት እንደሆነ ተናግረዋል።
እስራኤል በበኩሏ በመርከቦች ላይ እየደረሰ ያለው "የኢራን የሽብር ድርጊት" አለምአቀፍ የማሪታይ ደህንነትን የሚጎዳ ነው ብላለች።
ታጣቂዎቹ በቅርቡ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላት ያሏትን አንድ መርከብ በቁጥጥራቸው ስር ሲያውሉ የሚያሳይ ቪዲዮ መልቀቃቸው ይታወሳል።
አሜሪካ በጸጥታው ምክርቤት የቀረበው የተኩስ አቁም የውሳኔ ሀሳብ እንዳይጸድቅ ያደረገችው፣ ተኩስ አቁም የሚደረግ ከሆነ የሚጠቀመው ሀማስ ብቻ ነው ብላ ስለምታምን ነው።