በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሉ ልዩነቶች በውይይት መፈታት አለባቸው- የተመድ የጸጥታው ም/ቤት
ሀገራቱ ልዩነቶቻቸውን በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በተጀመረው ድርድር ሊጨርሱ እንደሚገባም ምክር ቤቱ አስታውቋል
ድርድሩ ሶስቱ ሀገራ በ2015 በካርቱም በተፈራረሙት የመርሆዎች ስምነት መሰረት ሊመራ ይገባልም ነው የተባለው
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በዛሬው እለት በታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአሜሪካ ኒውዮርክ ተሰብስቧል።
ስብሰባው ግብጽ እና ሱዳን ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ የተካሄደ ሲሆን ድምጽን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸው አምስቱን ቋሚ የምክር ቤቱን አባል ሃገራት ተወካዮች ጨምር ተለዋጭ የምክር ቤቱ አባል ሃገራት ተወካዮች ለውይይት በቀረበው የግድቡ ጉዳይ ላይ አቋማቸውን አንፀባርቀዋል።
የወቅቱን የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ሴሺኬዲን በመወከል በስብሰባው የተገኙት የዲ አር ኮንጎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚካሄደው ድርድር ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሶስቱንም ሃገራት እኩል እንደምታይ የገለፀችው ኬንያ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ራማፎዛ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር በነበሩበት ጊዜ የጀመሩትን የሶስትዮሽ የድርድር ሂደት እንዲቀጥሉ እና ሃገራቱ ጉዳዩን ከማቀጣጠል እንዲቆጠቡ ጠይቃለች።
ናይል የትብብር እንጂ የግጭት ምንጭ መሆን የለበትም ስትል በተወካይዋ በኩል ያስታወቀችው ኖርዌይ ጉዳዩ ፖለቲካዊ መፍትሔ ሊያገኝና በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ሊፈታ እንደሚገባ ይህንንም እንደምትደግፍ ገልጻለች።
ሩሲያ በበኩሏ የኃይል አማራጮች ሊወገዱ ይገባል ብላለች።
ውዝግቡን በፓለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መንገዶች በድርድር ከመፍታት ውጭ የተለየ አማራጭ አለ ብላ እንደማታምን የገለጸችም ሲሆን
የተሻለው አማራጭ የሶስትዮሽ ድርድር ነው ብላለች።
በዚህ የህብረቱን ተሳትፎ እንደምትደግፍ አስታውቃ ህብረቱ ጥረቱን እንዲያጠናክር ጠይቃለች።
ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ይበጃል ያለችም ሲሆን ይህንንም ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።
ሆኖም ምናልባትም ሃገራቱ ካልፈቀዱ በስተቀር በድርድሩ ሂደት የአሸማጋዮችና የታዛቢዎች መጨመር የሚጨምረው እሴት ይኖራል ብላ እንደማታምንም ነው ሞስኮ የገለጸችው።
“ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን እደግፋለሁም ነው ያለችው።
የሙሌቱን ሁኔታ የሚያሳዩ የሳታላይት ምስሎችን በማቅረብ ልትተባበር እንደምትችልም አስታውቃለች።
የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በወሳኝ ሁኔላይ መሆኑን በመጠቆም የቀጠናውን ሠላምና መረጋጋት ለመጠበቅ የሚያስችል ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ያለችው ደግሞ አሜሪካ ነች።
ዋሽንግተን ሶስቱ ሃገራት የግድቡን ጉዳይ ገንቢ በሆነ መንገድ ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት ደግፋለሁ ብላለች።
ሱዳንና ግብጽ ከግድቡ ጋር በተያያዘ የሚያነሷቸው ስጋቶች በህብረቱ ሊፈቱ እንደሚችሉና ህብረቱ ይህን የማድረግ አቅም አለው ብላ እንደምታምን ሆኖም የሃገራቱ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ እአስታውቃለች።
ሃገራቱ ከሚያካርሩ አተካራዎች ወጥተው ለመፍትሔ ሊሰሩና
የሶስዮሽ ድርድሩም በቶሎ ሊጀመር እንደሚገባም አሳስባለች።
ቻይና ሶስቱም ሀገራት ልዩነቶቻውን በውይይት ብቻ እንዲፈቱ እንደምትደግፍ የገለጸች ሲሆን፤ በ2015 በፈረሙት ስምምነት መርህ መሰረት ልዩነታውን እንዲፈቱም ጠይቃለች።
በስብሰባው የተገኙት የግብጽና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም
የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለም ጭምር የየሀገራቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ “ኢትዮጵያ ከስምነት ላይ ሳይደረስ የግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ጀምራለች፤ የጸጥታው ምክር ቤት እንዲያውቀው የምፈልገው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህጎችን በጣሰ መልኩ ሙሌቱን እያካሄደች ነው” ብለዋል።
ግብጽ ጉዳዩን ወደ ምክር ቤቱ ያመጣቸውም ለዚህ ነው፤ የጸጥታው ምር ቤት ይህንን ለማስቆም አስፈላጊውን ዓለም አቀፍ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል።
ግብጽ አሁንም ሁሉንም አካላት ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምነት ላይ እንደሚደረስ እምነት እነዳላት አስታውቀዋል።
ግድቡ የግብጽን እና ሱዳንን እንደማይጎዳ ማስተማመኛ እንፈልጋለን ሲሉም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሜህ ሹክሪ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ በሱዳን እና በግብጽ የሚቀርቡ ፕሮፖዛሎችን እና ሀሳቦች እንዲሁም ወዳጅ ሀገራ የሚያቀርቡትን መፍት ሀሳቦች በሙሉ ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች ሲሉም ተናግረዋል።
ሁሉንም ወደሚያስማማ ስምምነት መምጣት ካልተቻለ ግብጽ ብሄራዊ ጥቋም እና ዜጎቿን ደህንነት ለመጠበቅ ሁሉን አማራጭ ለመውሰድ ትገደዳለች ሲሉም ነው የተናገሩት።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርያም አል ሳዲቅ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ያለ ሱዳን እና ግብጽ እውቅና በራሷ ፍቃድ ግድቡን ሙሌት እያካሄደች ነው።
ባሳለፍነው ዓመት ለሁለቱም ሀገራት ሳታሳውቅ 5 በሊየን ሜትር ኪዩብ የውሃ ሙሌት አካሂዳለች፤ ይህም የአባይ ውሃ እንዲቀንስ አድርጓል፤ ዘንድሮም ክስምምነት ላይ ሳይደረስ የኢትዮጵያ የውሃ ሚኒስትር በጻፉት ደብዳቤ ብቻ ሁለተኛ ዙር ሙሌት መጀመሯን አሳውቃለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው ተግባር የሱዳንን የኤሌክትሪክ ምርት እና የግብርና ስራ ጎድቷል ብለዋል።
ሱዳን እና ግብጽ ኢትዮጵያ እያካሄደቸውብ ባለው የህዳሴ ግድብ ዙሪያ በተለይም በውሃ ሙሌቱ እና እንዴት መስራ አለበት የሚለው ላይ ህጋዊ ስምምነት እንዲፈረም እንደሚፈልጉም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ፤ ይህ ስብሰባ በዚህ መድረክ መካሄዱ የምክር ቤቱን ጊዜ ማባከን እንደሆነ ኢትየጵያ ታምናች፤ “በዚህ መድረክ ቀረበ የመጀመሪያው የውሃ ሚኒስትር ሳልሆን አልቀርም” ብለዋል።
“ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ስር ለሚካሄደው ድርድር ሙሉ ድጋፍ እና ክብር አላት፤ ልዩነቶች በውይይት እና በድርድር የሚፈቱ ናቸው ብላ ታምናለች” ሲሉም ተናግረዋል።
“በሀይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ፕሮጀክት ዙሪያ ነው የምንከራከረው፤ ግድቡ በጨለማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚገነባ መሆኑን ዓለም ሊገነዘበው ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።
“ግድቡ በኢትዮጵያውያን ላብ እና ደም ፋይናስ ምንጭ የሚገነባ መሆኑ በአይነቱ ልዩ ያደርገዋል” ያሉት ዶ/ር ኢነጂነር ሲለሺ፤ “በግድቡ ላይ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራ አለበት” ብለዋል።
“እንደ እድል ሆኖ ግብጽ እና ሱዳን በግድቡ ላይ ቅሬታ በማቅረባቸው እዚህ ተገኝተናል፤ ነገር ግን ሁለቱም ሀገራ በወንዙ ላይ አነስተኛ እና ትላልቅ ግድቦች አላቸው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ በውሃ ሀብቷ እንዳትጠቀም ይከለክላሉ” ብለዋል።
“የኢትዮጵያ 70 በመቶ የውሃ ሀብት ምንጭ የአባይ ውሃ ነው፤ ባንፈልግ እንኳ ይህንን ውሃ ሳንጠቀም መቆየት እና መቀመጥ አንችልም ” ብለዋል።
የተባሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የፖለቲካ እና የጸጥታ ጉዳይን ብቻ የሚመለከት ተቋም ነው፤ የውሃ ጉዳይ እንዲያይ መደረጉ አግባብ አይደለም ሲሉም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
“ኢትዮጵያውያን የአባይ ውሃ የመጠቀም መብት እንዳላቸው የጸጥታው ምር ቤት ሊገነዘበው ይገባል” ሲሉም አስታውቀዋል።
በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሚካሄደው ስብሰባ ሱዳን እና ግብጽ ከሰኔ 2020 ጀምሮ ውድቅ በማድረግ እያደናቀፉት እንደሚገኙም ነው ዶ/ር ኢነጂነር ስለሺ በቀለ የተናገሩት።
በቅርቡ በተገባደደው ሰኔ ወር በአፍሪከ ህብረት ሊቀ መንብረ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ሺስኬዲ በተጠራው ስብሰባ ላይ ሱዳን አለመገኘቷንም ለአብነት አንስተዋል።
የአባይ ጉዳይ አፍሪካ እና የአባይ ተፋሰስ ሀገራ ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ፤ የጸጥታው ምክር ቤት በህዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ ጣልቃ መግባት እንደሌለበትም ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ጥሪ አቅርበዋል።
“የኮሎኒያል ዘመን ስምምነቶች አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቷን እንዳትጠቀም እንቅፋት መሆን የለበትም፤ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ችግሩን ተረድተዋል” ያሉት ሚኒስትሩ ይህንን ለመቅረፍ እየሰሩ ነውም ብለዋል።
“አባይ ሁሉም የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ሀብት ነው፤ ስለዚህ ግብጽ እና ሱዳን በህዳሴ ግድብ ላይ ውሳኔ ከጸጥታው ምክር ቤት እንደማይመጣ ሊረዱ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ስለዚህ የህዳሴ ግድበ ጉዳይ በተፋሰሱ ሀገራ ትብብር እና ወይይት ብቻ እንደሆነ ሊያውቁ ይገባልም ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ይህንን አጀንዳ እዚሁ በመዝጋት ጉዳዩን ወደ ሚመለከተው የአፍሪካ ህብረት እንደሚመልሰውም ዶክተር ኢነጂነር ስለሺ በቀለ ጥሪ አቅርበዋል።