የዉኃ ሚንስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በጸጥታው ም/ቤት ስብሰባ ለመሳተፍ ኒውዮርክ ናቸው
የተመድ የጸጥታዉ ምክር ቤት በሕዳሴ ግድብ ዙርያ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በገጠሙት ዉዝግብ ላይ ለመነጋገር ዛሬ ይሰበሳባል
የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ሳሚ ሽኩሪ በስብሰባው ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል
የኢትዮጵያ ዉኃ፣መስኖና ኢነርጅ ሚንስትር ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚመክረው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) የጸጥታው ም/ቤት ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ሰኞ እለት ወደ ኒውዮርክ ማቅናታቸው ታውቋል፡፡
ሚኒስትሩ የፀጥታዉ ምክር ቤት ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በገጠሙት የግድቡ ዉዝግብ ላይ ለመነጋገር ዛሬ በሚያደርገው ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያን ይወክላሉ፡፡
አል ዐይን አማርኛ ከውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ዶ/ር ኢነጂነር ስለሺ በቀለ በስብስባው የኢትዮጵያን አቋም ያንጸባርቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያን ከሚወክሉት ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በተጨማሪ በስብሰባዉ ላይ የግብፅና የሱዳን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች የሚገኙ ይሆናል፡፡ የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ሳሚ ሽኩሪ በስብሰባው ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር መዘጋጀታቸውን ከወዲሁ እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡
ሻሚ ሱክሪ “የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት ዛሬ በሚያደርገዉ ስብሰባ፣ ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን በ6ወራት ዉስጥ አሳሪ ስምምነት ላይ የሚያደርስ ድርድር እንዲያደርጉ የሚያሳስብ ዉሳኔ ያሳልፍ ዘንድ ግብፅ ትጠይቃለች” ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱ ስብሰባዉ እንዲያደርግ የጠየቀችዉ የዓረብ ተወካዋ ቱኒዚያም ሶስቱም ሀገራት በአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና በተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ግብዣ፤ በ6 ወራት ዉስጥ ህጋዊ አስገዳጅ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የሚያስችል ድርድር እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ረቂቅ ዉሳኔ ለምክር ቤቱ አቅርባለች።
የስምምነቱ ረቂቅ “ኢትዮጵያ የውሃ ኃይል የማመንጨት አቅሟን የሚያረጋግጥ ... በተፋሰሱ ሀገራት የውሃ ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስ የሚከላከል” መሆን አለበት የሚል ነው፡፡
ኢትዮጵያ በተናጠል ከምታካሂደው የውሃ ሙሌት እንድትቆጠብ እንዲሁም ግብጽ እና ሱዳን የድርድር ሂደቱን አደጋ ላይ በሚጥልና በሚያደናቅፍ መልኩ ከሚያወጡት መግለጫ እንዲቆጠቡም የሚያሳስብ ነው ቱኒዝያ ያቀረበችው ረቂቅ፡፡
የግብፁ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚ ሽኩሪ እንደሚሉት የፀጥታዉ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ እንዲነጋገር ካይሮና ካርቱም የጠየቁት «ተጨባጭ ሥጋት» በመኖሩ ነዉ።
ሽኩሪ በስብሰባዉ በሚያደርጉት ንግግር ሶስቱ ሀገራት ለ10 ዓመታት ያደረጉት ድርድር ዉጤት አለማምጣቱን ለማስረዳት ማቀዳቸውንም የአሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል ።
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ለሁለተኛ ጊዜ መሙላት መጀመሯንም በፈረንጆቹ በ2015 የተደረገዉን ስምምነት የሚጥስ ነውም ነው ያሉት ሚኒሰትሩ ሳሚ ሹክሪ።
የፀጥታዉ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ማቀዱን ኢትዮጵያ “የአፍሪቃ ህብረት የሚሸመግለዉን ድርድርና ለአፍሪካዉያን ችግር አፍሪቃዊ መፍትሔ የመሻትን መርሕን የሚቃረን” በማለት ስትቃወም ቆይታለች።
በዛሬዉ ስብሰባ ላይ ከሶስቱ ሀገራት ሚንስትሮች በተጨማሪ በአፍሪቃ ቀንድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ኃላፊ እና የወቅቱ የአፍሪቃ ሕብረት ሊቀመንበር የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዲፕሎማት ለተሰብሳቢዎች ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።