የህዳሴው ግድብ የቴክኒክ ባለሙያዎች የሶስትዮሽ ድርድር ዳግም ተጀመረ
የግድቡ የቴክኒክ ባለሙያዎች ድርድር በግብጽ ካይሮ በመካሄድ ላይ ነው
ኢትዮጵያ የግድቡን የዘንድሮ ውሀ ሙሌት ወደ መስከረም አራዝሜያለሁ ማለቷ ይታወሳል
የህዳሴው ግድብ የቴክኒክ ባለሙያዎች የሶስትዮሽ ድርድር ዳግም ተጀመረ።
ኢትዮጵያ በድንበር ተሻጋሪው አባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በተለያዩ ምክንያቶች መቋረጡ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሶስትዮሽ ድርድር ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
በሱዳን እና በኢትዮጵያ የተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ለሶስትዮሽ ድርድር አለመቀጠል እና የግብጽ ተለዋዋጭ አቋም ማሳየት ለድርድሩ አለመሳካት ዋነኞቹ ምክንያቶች ነበሩ።
- ኢትዮጵያ እና ግብጽ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ በአራት ወራት ውስጥ ወደ ስምምነት ለመምጣት ተስማሙ
- የህዳሴው ግድብ እስከ መስከረም ውሀ እንደማይዝ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ
ከአንድ ወር በፊት በግብጽ ካይሮ በሱዳን ለተከሰተው ጦርነት እልባት ለመፈለግ በሚል በተካሄደው የጎረቤት ሀገራት መድረክ ላይ ለመሳተፍ ወደ ስፍራው ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እግረ መንገዳቸውን ከፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር መክረዋል።
ሁለቱ መሪዎች ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከልም የህዳሴው ግድብ ጉዳይ ዋነኛው ሲሆን በሶስት ወራት ውስጥ ዳግም ድርድር ለማድረግ መስማማታቸው ተገልጾ ነበር።
በዚህ ስምምነት መሰረትም የሶስቱ ሀገራት የህዳሴ ግድብ የቴክኒክ ባለሙያዎች በግብጽ መዲና ካይሮ ተገናኝተዋል።
የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን በዛሬው ውይይታቸው በቀጣይ ስለሚደረጉ ድርድሮች፣ የመወያያ አጀንዳዎች፣ እና በሶስቱ ሀገራት ልዩነቶች ዙሪያ እንደሚወያዩ ተገልጿል።
ከ12 ዓመት በፊት የተጀመረው ታላቁ የህዳሴው ግድብ ግንባታ 84 በመቶ ደርሷል የተባለ ሲሆን የግድቡ ሁለት ተርባይኖች ሀይል በማመንጨት ላይ ናቸው።
በጣልያኑ ሳሊኒ የግንባታ ተቋራጭ ኩባንያ እየተገነባ ያለው የህዳሴው ግድብ አራተኛው የግድቡ ውሀ ሙሌት ከቀናት በኋላ እንደሚጀመር ይጠበቃል።