ኢትዮጵያ እና ግብጽ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ በአራት ወራት ውስጥ ወደ ስምምነት ለመምጣት ተስማሙ
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት አልሲሲ በካይሮ በግድቡ ዙሪያ መክረዋል
ኢትዮጵያ የዘንድሮውን የህዳሴ ግድብ ውሀ ሙሌት ወደ መስከረም ተራዝሟል ማለቷ ይታወሳል
ኢትዮጵያ እና ግብጽ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ በአራት ወራት ውስጥ ወደ ስምምነት ለመምጣት ተስማሙ።
ግብጽ በሱዳን ያለውን ጦርነት ለማስቆም ያለመ ውይይት የጎረቤት ሀገራት መሪዎችን መጋበዟ ይታወሳል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የሱዳን ጎረቤት ሀገራት በመድረኩ ላይ ለመሳተፍ ወደ ካይሮ ያመሩ ሲሆን ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከውይይቱ በተጓዳኝ ከፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር መወያየታቸው ተገልጿል።
- ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር በካይሮ ተወያዩ
- ኢትዮጵያ ግብጽ ኃላፊነት ከጎደለው መግለጫዎቿና ማስፈራሪዎቿ እንድትታቀብ አሳሰበች
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ መወያየታቸው ሲገለጽ የግድቡ ውሀ አሞላል ደግሞ የመሪዎቹ ዋነኛ መወያያ እንደሆነ ተገልጿል።
በዚህ መሰረትም ኢትዮጵያ በግድቡ ውሀ አሞላል ዙሪያ ግብጽን እና ሱዳንን የመጉዳት ፍላጎት የላትም የተባለ ሲሆን በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ተጨማሪ ውይይቶችን ለማድረግ ስለመስማማታቸውም ተገልጿል።
መሪዎቹ ከህዳሴው ግድብ በተጨማሪ ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ባህላዊ ጉዳዮች ዙሪያ አብረው እንዲሰሩ እንደተስማሙ ተገልጿል።
የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ እንዳሉት " ሁለቱ ሀገራት በጋራ ከሰሩ ከህዝቦች ብልጽግና ባለፈ በአካባቢው ሀገራት ሰላም እንዲሰፍን እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ የሚሰሩባቸው እና የሚተባበሩባቸው አጀንዳዎች ይሰፋሉ" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ፣ ግብጽ እና ሱዳንም በህዳሴው ግድብ ውሀ አሞላል እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ያለባቸውን አለመግባባት በአራት ወራት ውስጥ በሚያደርጉት ውይይት ወደ ስምምነት ለመምጣት ተስማምተዋል ተብሏል።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ባሳለፍነው ሳምንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ የዘንድሮው የህዳሴ ግድብ ውሀ ሙሌት ወደ መስከረም ተራዝሟል ማለታቸው ይታወሳል።
እንደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ገለጻ ኢትዮጵያ የግድቡን ውሀ ሙሌት ወደ መስከረም ያራዘመችው ግብጽ እና ሱዳን ውሀ እስኪደርሳቸው በሚል ነው።
ከ12 ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 85 በመቶ ደርሷል ተብሏል።