የሕዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ቀጣይ ድርድር መቼ እና የት ይካሄዳል?
ኢትዮጵያ እና የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን ሊገናኙ ነው ተብሏል
ኢትዮጵያ እና ግብጽ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በአራት ወራት ውስጥ ወደ ስምምነት ለመምጣት መስማማታቸው ይታወሳል
የሕዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ቀጣይ ድርድር መቼ እና የት ይካሄዳል?
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በወቅታዊ የዲፕሎማሲ ስራዎች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ መግለጫ ከሰጡባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ አንዱ ሲሆን በቀጣይ ስለሚካሄዱ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ባሳለፍነው ሳምንት ግብጽ በሱዳን ጉዳይ ለመምከር በካይሮ በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ባመሩበት ወቅት ከግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ መወያየታቸው ይታወሳል።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎችም በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በአራት ወራት ውስጥ ወደ ስምምነት ለመምጣት ተስማምተውም ነበር።
ይህን ስምምነት መነሻ በማድረግም የህዳሴው ግድብ ውይይት መቼ፣ የት እና እንዴት ይካሄዳል? በሚል ከጋዜጠኞች ለአምባሳደር መለስ ዓለም ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።
አምባሳደር መለስም " በግድቡ ዙሪያ በካይሮ በተደረሰው ስምምነት መሰረት የሀገራቱ የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን ተገናኝቶ ድርድሩ የት ፣ መቼ እና እንዴት ይካሄዳል? እሚለውን ይወስናሉ" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የሀላፊነት ቦታዎች ላይ እንዲወከሉ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከቀናት በፊት በኬንያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚዎች ኢትዮጵያ በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ደመቀ መኮንን ተወክላ መሳተፏ ተገልጿል።