ቀጣዩ የህዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገለጸ
የኢትዮጵያ ፣ግብጽ እና ሱዳን የህዳሴው ግድብ ባለሙያዎች ቡድን በካይሮ የጀመሩት ድርድር ተጠናቋል
የካይሮው ውይይት የሶስትዮሽ ድርድሩ ቀጣይ አቅጣጫዎች ምን መምሰል አለበት እሚለው ዋነኛ ጉዳይ ነበር ተብሏል
ቀጣዩ የህዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገለጸ።
የህዳሴው ግድብ የቴክኒክ ባለሙያዎች የሶስትዮሽ ድርድር ባለፉት ሁለት ቀናት በግብጽ ካይሮ መካሄዱን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል።
ኢትዮጵያ በድንበር ተሻጋሪው አባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በተለያዩ ምክንያቶች መቋረጡ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሶስትዮሽ ድርድር ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
በሱዳን እና በኢትዮጵያ የተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ለሶስትዮሽ ድርድር አለመቀጠል እና የግብጽ ተለዋዋጭ አቋም ማሳየት ለድርድሩ አለመሳካት ዋነኞቹ ምክንያቶች ነበሩ።
ከአንድ ወር በፊት በግብጽ ካይሮ በሱዳን ለተከሰተው ጦርነት እልባት ለመፈለግ በሚል በተካሄደው የጎረቤት ሀገራት መድረክ ላይ ለመሳተፍ ወደ ስፍራው ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እግረ መንገዳቸውን ከፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር መክረዋል።
ሁለቱ መሪዎች ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከልም የህዳሴው ግድብ ጉዳይ ዋነኛው ሲሆን በሶስት ወራት ውስጥ ዳግም ድርድር ለማድረግ መስማማታቸው ተገልጾ ነበር።
በዚህ ስምምነት መሰረትም የሶስቱ ሀገራት የህዳሴ ግድብ የቴክኒክ ባለሙያዎች በግብጽ መዲና ካይሮ ተገናኝተው መክረዋል።
የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን በካይሮ ውይይታቸው በቀጣይ ስለሚደረጉ ድርድሮች፣ የመወያያ አጀንዳዎች፣ እና በሶስቱ ሀገራት ልዩነቶች ዙሪያ መወያየታቸው ተገልጿል።
የሶስቱ ሀገራት የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን ቀጣይ ውይይታቸውን በአዲስ አበባ መስከረም ወር ውስጥ ለማካሄድ መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል።
በውይይቱ ላይ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ፣ ኢንጅነር ጌድዮን አስፋው እና ሌሎች የህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ የቴክኒክ ቡድን አባላት ኢትዮጵያን ወክለው ተሳትፈዋል።
ከ12 ዓመት በፊት የተጀመረው ታላቁ የህዳሴው ግድብ ግንባታ 84 በመቶ ደርሷል የተባለ ሲሆን የግድቡ ሁለት ተርባይኖች ሀይል በማመንጨት ላይ ናቸው።
በጣልያኑ ሳሊኒ የግንባታ ተቋራጭ ኩባንያ እየተገነባ ያለው የህዳሴው ግድብ አራተኛው የግድቡ ውሀ ሙሌት ከቀናት በኋላ እንደሚጀመር ይጠበቃል።