ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እስካሁን ከ163 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉ ተገለፀ
ግደቡ በዓመት 15 ሺህ 760 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ማመንጨት ይችላል
የግድቡ አጠቃላይ የግንባታ ሂደት ከ84 በመቶ በላይ ደርሷል
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሁን እስከ ደረሰበት የግንባታ ሂደት ከ163 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት የግድቡ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ገለጹ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አንድ ተርባይን በዛሬው እለት በ375 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ጀምሯል።
የኃይል ማመንጨት ማስጀመሪያ ላይ ንግግር ያደረጉት የህዳሴ ግድብ ፐሮጀክት ዋና ስረ አስኪያጅ ኢንጂነር ከፍሌ ሆሮ፤ “በእኛ ትውልድ የአባቶቻችንን ህልም ማሳካት በመቻላችን ከፍተኛ ኩራት ይሰማናል” ብለዋል።
ግድቡ በ13 ተርባይኖች እንዳለው የገለጹት ስራ አስኪያጁ፤ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት አቅም ያለው መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ በዓመት 15 ሺህ 760 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ያመነጫል ብለዋል።
የግድቡ 13 ተረባይኖች ከዋናው ግሪድ ጋር በ500 እና 400 ኪሎ ቮልት የኃይለ ማስተላፊያ የሚገናኙ መሆኑን ኢንጂነር ክፍሌ ተናግረዋል።
ግድቡ ሙሉ በሙሉ ሙኃ መያዝ ሲጀምር በአጠቃላይ 17 ሚሊየን ሜትር ኩብ ዋኃ ይይዛል ያሉ ሲሆን፤ ይህም ከጣና ሃይቅ በሁለት ተኩል እጥፍ ይበልጣል፤ ከኢትዮጵያም ትልቁ ሰው ሰራሽ ኃይቅ ይሆናል ብለዋል።
በግድቡ ግንባታ አሁን ላይ 7000 ኢትዮጵያውያን እየተሳተፉ ነው ያሉት ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፤ ወደ 500 የሚጠጉ ከ40 በላይ ሀገራት የተውጣጡ የውጭ ሀገራት ዜጎቸ በግንባታው ላይ እየተሳተፉ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እስኪደርስ 10 ሺህ ሰራተኞች መሰተፋቸውንም ገልጸዋል።
ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ አክለውም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጠቃላይ ግንባታ ከ84 በመቶ በላይ መድረሱንም ነው የገለጹት።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሲቪል ግንባታውን እያካሄደ የሚገኘው የጣሊያኑ ሳሊኒ ኩባንያ ስራ አስኪያጅ ፔትሮ ሳሊኒ፤ የዓበይ ወንዝ ፈጣሪ በተለየ መልኩ ለኢትዮጵያ የሰጣት ነው ብለዋል።
አባይ የኢትዮጵያ ነጭ ነዳጅ ነው ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ጠላቶች የመጀመሪያው ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በ2003 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከትልልቅ የአገሪቱ ብሔራዊ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው።