“ሁለተኛው ዙር ሙሌት ሲጠናቀቅ ግድቡ ራሱን መጠበቅ ይጀምራል”- ኢ/ር ጌድዮን አስፋው
የግድቡ ሁለት ተርባይኖች በነሃሴ መጨረሻ ኃይል ማመንጨት ይጀምራሉ መባሉ ይታወሳል
“የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስራ የአባይ ጉዳይን ከፊት ያስቀደመ ነው”- ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌቱ ሲጠናቀቅ እራሱን መጠበቅ እንደሚችል ኢንጅነር ጌድዮን አስፋው ተናገሩ።
ትኩረቱን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያደረገ ውይይት በደብረብርሃን ዩንቨርሲቲ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የህዳሴው ግድብ ብሔራዊ ተደራዳሪ እና የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢው ኢንጅነር ጌድዮን አስፋው በዚህ መድረክ ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያዊያን ግድቡን ወደማይቀለበስበት ደረጃ አድርሰውታል ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ በሶስት ደረጃ እየተሰራ ነው ያሉት ኢንጂነር ጌዲዮን ግድቡ አሁን ከ80 በመቶ በላይ ተጠናቋል ሲሉ ሁለተኛው ሙሌት ሲጠናቀቅ 18 ነጥብ 4 ቢሊየን ሜትሪክ ኪዮብ ውሃ መሸከም ስለሚችል ግድቡ ራሱን በሚጠብቅበት ደረጃ ይደርሳል ብለዋል።
በአባይ ወንዝና በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ በርካታ ጥናቶችን እየሰሩ የሚገኙት በአባይ ወንዝ ተመራማሪ እና ተደራዳሪ ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስራ የአባይ ጉዳይን ከፊት ያስቀደመ ነው ብለዋል።
ሌላኛው የአባይ ወንዝ እና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ ኢብራሂም ደግሞ የግብፅ እና ሱዳን ዲፕሎማቶች የሚያነሱት መደራደሪያ ሀሳብ የኢትዮጵያን በራስ ሀብት የመጠቀም መብትን የሻረ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የሁለቱ አገራት በአባይ ወንዝ ላይ ያላቸው አቋም በጋራ የመጠቀም መብትን የማያከብር በመሆኑ ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው መናገራቸውንም ኤፍቢሲ ዘግቧል።
አምባሳደር ኢድሪስ ኢብራሂም የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተደጋጋሚ የሚያነሷቸው ሀሳቦች የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ለማስከበር ያለሙ እና ከድርድር ያፈነገጡ መንገዶችን እየተጠቀሙ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የህዳሴ ግድብ ውሃ መያዝ መርሃ ግብርን ለማካሄድ የክረምቱን መግባት በመጠባበቅ ላይ ስትሆን ከነሃሴ ወር መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ በሁለቱ ተርባይኖች 700 ሜጋ ዋት ሀይል ማመንጨት እንደምትጀምር ማሳወቋ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባሳለፍነው ሳምንት በሚቀጥለው ዓመት 100 አነስተኛ እና መካከለኛ ግድቦችን እንገነባለን ሲሉ መናገራቸው አይዘነጋም።