ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ዛሬ በጅቡቲ ጉብኝት አድርገው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል
የግብፁ ፕሬዝደንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ዛሬ ጂቡቲን ጎበኙ፡፡
አል ሲሲ ከጂቡቲ ፕሬዝደንት እስማኤል ኦማር ጌሌ ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸው ተገልጿል።
መሪዎቹ ሽብርተኝነትን በጋራ ለመከላከል ስለሚቻልበት ሁኔታ መምከራቸው የተገለጸም ሲሆን ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ በመገንባት ላይ ባለችው በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ተወያይተዋልም ተብሏል፡፡
መሪዎቹ በተለይም በቀይ ባህር አካባቢ ሽብርተኝነትን በጋራ መከላከል የሚያስችሉ ስራዎችን ለመስራት እንደተስማሙ ነው የተገለጸው።
በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ባደረጉት ውይይት ፕሬዝዳንት ሲሲ ፍትሀዊ እና ግልጽ ስምምነት ሳይኖር ኢትዮጵያ ግድቡን ለሁለተኛ ጊዜ መሙላት የለባትም የሚል አቋም ማንጸባረቃቸው ተሰምቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግብፅ እና ኬንያ በትናንትናው እለት ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ በናይሮቢ የተፈረመው ስምምነት ዓላማ የሁለቱን ሀገራት የጋራ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚደረገው የሁለትዮሽ ትብብር አካል ነው ተብሏል፡፡
ግብፅ ከኬንያ ጋር ያደረገችው ወታደራዊ ስምምነት እ.ኤ.አ. በ2021 በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ ሀገራት ጋር ያደረገችው አራተኛ ስምምነት ነው፡፡
ከኬንያ በተጨማሪ ከሱዳን፣ ከኡጋንዳ እና ከብሩንዲ ጋርም ወታደራዊ ስምምነቶችን ፈርማለች፡፡
በተያያዘ ዜና ግብፅ እና ሱዳን በትናንትናው ዕለት ለ 6 ቀናት የሚቆይ ሁለገብ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ በሱዳን ጀምረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ ጉዳይ ከሁለቱ ሀገራት ጋር ውጥረት ውስጥ በምትገኝበት ወቅት የሚካሔደው ይህ ልምምድ ፣ የናይል ጠባቂዎች (Nile Protectors/ናይል ፕሮቴክተርስ) የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
ከግድቡ በተጨማሪ ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር ጉዳይም ከፍተኛ አለመግባባት ውስጥ የሚገኙ መሆኑ ይታወቃል፡፡