የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ ጀርመን ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት እንድትገድብ ጥሪ አቅርቧል
የጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ቻይናን እንደሚጎበኙ አስታወቁ።
የጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ከሁለት ሳምንት በኋላ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ቤጂንግ እንደሚጓዙ ሮይተርስ ዘግቧል።
ኦላፍ ሾልዝ ወደ ቤጂንግ የሚያቀኑት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ቡድናቸው ይዘው እንደሆነ በዘገባው ላይ ተጠቁሟል።
ጀርመን ከቻይና ጋር ጥብቅ የንግድ ግንኙነት ካላቸው የአውሮፓ ሀገራት መካከል ዋነኛዋ ስትሆን ይህ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትስስሯ ግን በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት እንዳልተወደደላት ተገልጿል።
የቻይናው የሎጅስቲክ ኩባንያ ሲስኮ በአውሮፓ ካሉ ግዙፍ ወደቦች መካከል አንዱ የሆነው ሀምቡርግ ወደብን የ35 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ የወጣውን ጨረታ አሸንፏል።
ይሄንን ተከትሎም የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ጀርመን ለቻይናው ሲስኮ ኩባንያ የሀምቡርግ ወደብን ሽያጭ እንድትሰርዝ በመወትወት ላይ ናቸው።
የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጀርመን የአውሮፓን ሀብት ለቻይና እንሳትሸጥ ጥሪ አቅርበዋል።
በኦላፍ ሾልዝ የሚመራው የጀርመን መንግስት በሀምቡርግ ወደብ ድርሻ ሽያጭ ዙሪያ ለሁለት መከፈሉ ተገልጿል።
የተወሰኑት የጀርመን ፖለቲከኞች የቻይናው ሲስኮ ኩባንያ ለሀምቡርግ ወደብ ያቀረበው ገንዘብ እጅግ ብዙ ነው ሽያጩ ሊጸድቅ ይገባል በማለት ላይ ናቸው።
ቀሪዎቹ ደግሞ ጀርመን ከአውሮፓ ህብረት ፍላጎት በተቃራኒ በመቆም ሀምቡርግን ለቻይና ልትሸጥ እንደማይገባ ተናግረዋል።
የኦላፍ ሾልዝ መንግስት በዚህ ጉዳይ ጫና ውስጥ መግባቱ ሲገለጽ ከሁለት ሳምንት በኋላ ወደ ቤጂንግ በማምራት ከፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ ጋር እንደሚወያይ ይጠበቃል።
የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካንን ጨምሮ የቡድን ሰባት ሀገራት የቻይናን ተጽዕኖ ለመመከት 300 ቢሊዮን ዶላር በጀት መመደባቸው አይዘነጋም።