ኦላፍ ሾልዝ ለ16 ዓመታት የጀርመንን የመሩትን አንጌላ ሜርክልን በመተካት የሀገሪቱ መራሄ መንግስት ሆነዋል
ኦላፍ ሾልዝ ለ16 ዓመታት የጀርመን መራሄተ መንግስት በመሆን ያገለገሉትን አንጌላ ሜርክልን በመተካት የሀገሪቱ መራሄ መንግስት ሆኑ።
ኦላፍ ሾልዝ የሜርክል ምክትል እንዲሁም የፋይናንስ ሚኒስትር ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩ ሲሆን አሁን የሀገሪቱ መንግስት መሪ ሆነዋል።
ሾልዝ የመጀመሪያው የሃምቡርግ ከተማ ከንቲባ የነበሩ ሲሆን፤ ከአውሮፓውያኑ 2009 እስከ 2019 የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል መሪ ሆነው አገልግለዋል።
ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ፣ ግሪን እና ሊብራል ፍሪ ዴሞክራቲክ ያደሩት ጥምረት የአንጌላ ሜርክልን የ16 ዓመታት የቤተ መንግስት ቆይታ ቋጭቶታል።
ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ የሜርክልን ክርስቲያን ዲሞክራቲክ ዩኒየን ፓርቲን በምርጫ ካሸነፈ ከሁለት ወር በኋላ ኦላፍ ሾልዝ የጀርመን መራሄ መንግስት ሆነዋል።
አዲሱ መራሄ መንግስት መደበኛ በሆነ መልኩ በቡደስታግ (በሀገሪቱ ፓርላማ) የተሾሙ ሲሆን በፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተር ስታይማየር ፊት ቃለ መሃላ ይፈጽማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሾልዝን ወደ መራሄ መንግስትነት ያመጣው በፈረንጆቹ መስከረም 26 የተካሄደው ምርጫ ነው።