የጀርመን መራሄ መንግስት ከነዳጅ ጋር በተያያዘ የገልፍ ሀራትን እየጎበኙ ነው
ሳውዲ አረቢያ፣ አረብ ኢምሬት እና ኳታር በኦላፍ ሾልዝ እየተጎበኙ ያሉ ሀገራት ናቸው
ጀርመን በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ምክንያት እየተፈተኑ ካሉ ሀገራት መካከል ዋነኛዋ ናት
የጀርመኑ መራሄ መንግስት ከነዳጅ ጋር በተያያዘ የአረብ ሀራትን እየጎበኙ ነው፡፡
የአውሮፓ ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው ጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ያጋጠማቸውን ነዳጅ ችግር ለመፍታት በሚል ሶስት የባህረ ሰላጤ ሀገራትን በመጎብኘት ላይ ናቸው፡፡
መራሄ መንግስቱ በዛሬው ዕለትም በሪያድ ከሳውዲ አልጋወራፍ መሀመድ ቢን ሳልማን ጋር የመከሩ ሲሆን የውይይት አጀንዳቸው ነዳጅ እንደሆነ የጀርመን ድምጽ ዘግቧል፡፡
ሩሲያ እና ዩክሬን ወደ ጦርነት መግባታቸውን ተከትሎ በሞስኮ ነዳጅ ላይ ጥገኛ የሆነችው ጀርመን የነዳጅ አቅርቦቷ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡
በዚህም ምክንያት ጀርመን ለነዳጅ ድጎማ በሚል ከ60 ቡሊዮን በላይ ዩሮ ያወጣች ሲሆን በርካታ ተቋማት ሀገራቸው በነዳጅ አቅርቦት ላይ እንዲሰራ በመወትወት ላይ ናቸው፡፡
ይሄንን ተከትሎም በርሊን ኢኮኖሚዋ እንዳይጎዳ የነዳጅ አቅርቦት ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ለማግኘት ጥሮችን በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
የሀገሪቱ መራሄ መንግስትም በነዳጅ የበለጸጉ የአረብ ሀገራት ነዳጃቸውን ወደ በርሊን ሊልኩ በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ለመወያየት ወደ ቦታው አምርተዋል፡፡
መራሄ መንግስቱ ሾልዝ ከሳውዲ አረቢያ በመቀጠል ወደ አቡዳቢ እና ዶሃ በማቅናት ከሁለቱ ሀገራት ፕሬዝዳንቶች ጋር እንደሚወያዩ ዘገባው አክሏል፡፡
ኦላፍ ሾልዝ ከሶስቱ ሀገራት ፕሬዝዳንቶች ጋር ከነዳጅ አቅርቦት በተጨማሪ በሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ዙሪያ እንደሚመክሩ ተገልጿል፡፡
ሩሲያ ጦሯን ለልዩ ዘመቻ በሚል ወደ ዩክሬን መላኳን ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ነዳጅ ላይ ማዕቀብ እና የመሸጫ ዋጋ ትመና የጣለ ሲሆን ሩሲያ በበኩሏ ማዕቀቡን ካላነሳችሁ አንድም ጠብታ ነዳጅ አልክም ማለቷ ይታወሳል፡፡