የጀርመን መራሄ መንግስት “ሩሲያ ከዩክሬን ምድር ሙሉ በሙሉ ለቃ እንድትወጣ” ፑቲንን ጠየቁ
ኦላፍ ሾልዝ “የዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያ ደህንነት እንዲጠበቅ” ሲሉም ፑቲንን አሳስበዋል
ኦላፍ ሾልዝ፤ ፑቲን በተቻለ ፍጥነት ወደ “ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ” እንዲመጡ አሳስበዋል
የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ “ሩሲያ ከዩክሬን ምድር ሙሉ በሙሉ ለቃ እንድትወጣ” ፑቲንን ጠየቁ፡፡
ኦላፍ ሾልዝ ከፑቲን ጋር በነበራቸው 90 ደቂቃ በፈጀ የስልክ ቆይታ ፤ “ፑቲን በተቻለ ፍጥነት ተኩስ አቁመው ወደ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንዲመጡና ወታደራቸው ሙሉ በሙሉ ከዩክሬን ምድር በማውጣት የዩክሬን ግዛት ሉዓላዊነት እንዲያከብሩ” ማሳሰባቸው ቃል አቀባያቸው ስቴፈን ሃበስተሬት አስታውቋል፡፡
ኦላፍ ሾልዝ በተጨማሪም ሩሲያ በተደጋጋሚ የምትወቅሰውን እህል ከዩክሬን ወደ ውጭ የመላክ ጉዳይ የተደረሰውን የእህል ስምምነት እንድታከብር ፑቲንን መናገራቸውም ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ፑቲን የእህል ስምምነቱን እንዳያጣጥሉ እና ሙሉ በሙሉ መተግበሩን እንዲቀጥሉም የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ተማጽነዋል፡፡
ኦላፍ ሾልዝ አሁን ላይ የጦርነቱ የስህበት ማዕከል ስለሆነው የዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ደህንነት ጉዳይ በተመለከተም ለፑቲን ጥያቄ አንስተው ተወያይተዋል፡፡
በዚህም የጀርመኑ መሪ ፑቲን "ምንም አይነት መባባስ እንዲያስወግዱና በዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የተመከሩትን እርምጃዎች (ነጻ ቀጠና እንዲቋቋም) ሙሉ በሙሉ እንዲተገብሩ" ጠይቀዋል።
የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ከፑቲን ጋር ዘለግ ያለ ቆይታ ያደረጉት፤ ሞስኮ በርሊን ለዩክሬን የጦር መሳሪያዎችን በመላክ ቀይ መስመር እየጣሰች ነው የሚል ማስጠንቀቅያ በሰጠቀችበት ማግስት መሆኑ ነው፡፡
በጀርመን የሩሲያ አምባሳደር ሰርጌይ ናቼቭ ፤ የዩክሬን መንግስት ጀርመን ስሪት አውዳሚ ጦር መሳሪያዎችን እየታጠቀ መሆኑ ሀቅ ነው ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
የጦር መሳሪያዎች በሩሲያ ጦር ላይ ብቻ ሳይሆን በዶንባስ ክልል በሚገኙ ንጹሃን ዜጎችን ለማጥቃት እየዋሉ እንደሆነም ነበር የተናገሩት አምባሳደሩ፡፡
የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ሀገራቸው ለዩክሬን አዲስ የጦር መሳሪያ ልታበረክት መሆኑን እና በቅርቡ እንደሚላክላት መናገራቸው ይታወሳል።
ኦላፍ ሾልዝ ሃምሌ ላይ በዩክሬን ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ሀገራቸው ዩክሬንን ለማገዝ ዝግጁ መሆኗን ለፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በገልጸውላቸዋል።
ጀርመንም ለዩክሬን ጦር መሳሪያ ለማቅረብ በሚል ፖሊሲ እስከ ማሻሻል ደርሳ እንደነበረ ይታወሳል።
ሩሲያም በተለያዩ ጊዜያት ከምእራባውያን ለዩክሬን ያበረከቷቸው የረጅም ርቀት ሮኬትን ጨምሮ ይለያዩ የጦር መሳሪያዎችን አወደምኩ ማለቷ አይዘነጋም።