ጀርመናውያን ሜርክልን የሚተካውን ሰው ለመምረጥ ድምፅ እየሰጡ ነው
የጀርመን ቡንደስታግ ተብሎ ለሚጠራው የሀገሪቱ የታችኛው ምክር ቤት ምርጫ እየተካሄደ ነው
ኦላፍ ሾልዝ፣ አርሚን ላሼት እና አናሌና ቤርቦክ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልን ስፍራ ለመያዝ እየተፎካከሩ ነው
ጀርመናውያን ሀገሪቱን ለ16 አመታት አመታት መራሒተ መንግሥት ሆነው ያገለገሉትን አንጌላ ሜርክልን የሚተካ ሰው ለመወሰን ድምጽ እየሰጡ ነው።
ጀርመናውያን በዛሬው እለት ከማለዳው ጀምሮ የጀርመን ቡንደስታግ ተብሎ ለሚጠራው የአገሪቱ የታችኛው ምክር ቤት አባላት ለመምረጥ ድምጽ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
በምርጫው 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች 6 ሺህ 211 እጩዎች ያቀረቢ ሲሆን፤ ከእጩዎቹ መካከል 2 ሺህ 024 ሴቶች መሆናቸውን ዶቸ ዌሌ ዘግቧል።
ከጀርመን 60 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች 40 በመቶው ለመምረጥ በቂ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፤ መራጮች በድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት መምረጥ የጀመሩት ዛሬ እሁድ ነው።
ይሁንና በፖስታ ቀደም ብለው ድምጽ የሰጡባቸውን ወረቀቶች የላኩ ዜጎች በመኖራቸው ምርጫው የተጀመረው ቀደም ብሎ እንደሆነም ዘገባው አመላክቷል።
የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በበርሊን የድምጽ መስጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምጽ መስጠታቸውንም ዘገባ ያመላክታል።
ለ16 አመታት አመታት ጀርመንን የመሩትን መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክልን ለመተካት ከፍተኛ ፉክክር እየተካሄደ መሆኑም ነው የተነገረው።
በዚህም መሰረት ከሶሻል ዴሞክራቶቹ ኦላፍ ሾልዝ፣ ከክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት አርሚን ላሼት እንዲሁም ከግሪን ፓርቲ ወይም አረንጓዴ ፓርቲ አናሌና ቤርቦክ ስፍራውን ለመያዝ በእጩነት ቀርበዋል ነው የተባለው።