ፖለቲከኛው አሁን ላይ ከሞስኮ 100 ኪሎ ሜትር በሚርቅ ቦታ እስር ላይ ነውም ተብሏል
የጀርመኗ መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክል፤ በሩሲያ መንግት የታሰረው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ አሌክስ ናቫልኒ እንዲትፈታ ጠየቁ።
መራሄተ መንግስቷ በሞስኮ የነበራቸውን ጉብኝት ከማጠናቀቃቸው አስቀድሞ ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ናቫልኒ መጠየቃቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል። ናቫልኒ የዛሬ ዓመት በነርቭ ጥቃት ተደርጎበት በጀርመን ሀኪሞች ድኖ እንደነበርም ሲገለጽ ቆይቷል።
በክሬሚሊን ቤተ መንግስት በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሜርክል ፕሬዝዳንት ፑቲን ናቫልኒን ከእስር እንዲለቁት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በበኩላቸው ናቫልኒ የታሰረው በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እንዳልሆነ አስታውቀዋል። ይልቁንም ከወንጀሎች ጀርባ እጁ እንዳለበት ፕሬዝዳንት ፑቲን ለአንጌላ ሜርክል መግለጻቸው ተዘግቧል።
ፕሬዝዳንቱ፤ ናቫልኒ በተገቢው ሁኔታ እንዲያዝ የሩሲያን ሕግ ተርጓሚ አካል ሊጠይቁ እንደሚችሉ ያነሱ ሲሆን ሞስኮ ሁሉነወ አቀፍ የፖለቲካ ስርዓት እንዳላትም ጠቁመዋል ነው የተባለው።
መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ምንም እንኳን ጀርመን እና ሩሲያ ጥልቅ ልዩነቶች ቢኖሯቸውም ተገናኝቶ ውይይት ማድረጉ ጠቃሚ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ልክ ምስራቅ ጀርመን እንዳደጉት አንጌላ ሜርክል ሁሉ የቀድሞው የኬጂቢ ስለላ ተቋም ሰራተኛ እና የአሁኑ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም በአንድ ወቅት ምስራቅ ጀርመን ነበሩ።
ምንም እንኳን ሁለቱ መሪዎች አንድ ቦታ የነበሩ ቢሆንም የተነጋገሩት ግን በየራሳቨው ሀገር ቋንቋ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ሁለቱ መሪዎች በተደጋጋሚ የመገናኘት ዕድል ያገኙ ሲሆን በሳይበር ጥቃት እንዲሁም በዩክሬን እና በሶሪያ ምክንያት አለመግባባቶች ውስጥ ሲገቡ እንደነበር ይታወሳል።
አንጌላ ሜርክል በ 16 ዓመታት የሥልጣን ቆይታቸው ፕሬዝዳንት ፑቲንን 16 ጊዜ አግኝተዋቸዋል ተብሏል፡፡ ምንም እንኳን መሪዎቹ ብዙ ጊዜያትን ቢገናኙም በበርካታ ጉዳዮች አለመግባባት ውስጥ ሲገቡ እንደነበር የየሚታወስ ነው።
የአሁኑ የመሪዎቹ ግንኑነትም በፖለቲከኛው ናቫልኒ ምክንያት አለመግባባት እንደገጠመው ተገልጿል። አሌክስ ናቫልኒ አሁን ላይ ከሞስኮ ምስራቃዊ አቅጣጫ 100 ኪሎ ሜትር በሚርቅ እና ፖክሮቭ በተሰኘ ቦታ በእስር ላይ ይገኛል።