ጀርመን የ300 ሺህ ሰራተኞች እጥረት እንደገጠማት ገለጸች
ጀርመን የገጠማት የሰራተኞች እጥረት ቶሎ ካልተፈታ እጥረቱ ወደ 1 ሚሊዮን ከፍ ሊል ይችላል ተብሏል
አገሪቱ የገጠማትን የሰራተኛ እጥረት ለመፍታት ከውጭ አገራት ለማስገባት አቅዳለች
ጀርመን የ300 ሺህ ሰራተኛ እጥረት እንደገጠማት ገለጸች፡፡
የአውሮፓ ባለ ፈርጣማ የኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ጀርመን የሰራተኞች እጥረት እንደገጠማት የአገሪቱ ምክትል ቻንስለር ሮበርት ሀቤክ ተናግረዋል፡፡
አገሪቱ የገጠማት የሰራተኛ እጥረት ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ላይ ሲሆን ይሄንን ችግር ለመፍታት አዲስ ፖሊሲ እንደሚያስፈልጋትም ምክትል ቻንስለሩ አክለዋል፡፡
የሰራተኛ እጥረቱ በጀርመን ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል ያሉት ምክትል ቻንስለሩ በተለይም የአገሪቱን የሀይል ሽግግር አደጋ ውስጥ እንደሚያስገባው ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ 300 ሺህ የስራ እድሎች አሉ ይህ እጥረት በቀጣይ ወደ አንድ ሚሊዮን ከፍ እንደሚልም ሮበርት ሀቤክ አክለዋል፡፡
ይሄንን የስራ እድሎች በሰራተኞች ካልሸፈንን ጀርመን ከፍተኛ የምርት እጥረት እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ እጥረቶች ያጋጥማታል ብለዋል፡፡
የሰራተኛ እጥረቱን ለመፍታት በቤተሰብ ደረጃ ሳይቀር ስልጠናዎችን በመስጠት፣ ከውጭ አገራት በህጋዊ መንገድ በማምጣት መፍታት ይጠበቅብናል ሲሉም ምክትል ቻንስለሩ ገልጸዋል፡፡
ጀርመን አሁን ላይ የገጠማት የስራ አይነቶች ምህንድስና፣ የእደ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የእንክብበካቤ ሙያተኞች እና ሌሎችም ሙያዎች መሆኑን አስታውቃለች፡፡
እንደ ጀርመን የኢኮኖሚ ተቋም ትንበያ ከሆነ በዚህ ዓመት በጀርመን የ300 ሺህ ሰራተኞች እጥረት የሚያጋጥም ሲሆን ከዚህ የበለጠ ቁጥር ደግሞ በጡረታ ከስራ ዓለም ይገለላሉ፡፡
የጀርመን የሰራተኛ እጥረቱ በፈረንጆቹ 2029 ዓመት ወደ 650 ሺህ ከፍ እንደሚል የተነበየው ይሄው ተቋም በ2030 ደግሞ እጥረቱ ወደ 5 ሚሊዮን ያሻቅባል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በጀርመን ላጋጠመው የሰራተኛ እጥረት ላለፉት ዓመታት ዝቅተኛ የውልደት ምጣኔ በመመዝገቡ እና የስደተኞች ፖሊሲ ዋነኛ ምክነንያቶች ናቸው ተብሏል፡፡
አዲስ የተመሰረተው የጀርመን መንግስት ሰራተኞች በስራ ላይ የሚቆዩበትን ጊዜ ለመጨመር የአንድ ሰዓት የስራ ላይ ክፍያን ወደ 12 ዩሮ ከፍ ያደረገ ቢሆንም ጡረታ መውጣት በሚፈልጉ ዜጎች እና በህይወት የመቆየት ጊዜ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል በመባል ላይ ነው፡፡