ኤርትራ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አውሮፕላን በአየር ክልሏ እንዳያለፍ ከለከለች
ወደ ጂቡቲ በማምራት ላይ የነበረው የጀርመን አውሮፕላን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተመልሶ ለማረፍ ተገዷል
የጀርመን የየውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በጂቡቲ፣ ኬንያና ደቡብ ሱዳን ጉብኝት ለማድረግ እቅድ ነበራቸው
ኤርትራ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌላ ባየርቦክ አሳፍሮ ሲጓጓ የነበረን አውሮፕላንን ከአየር ክልሏ ማስወጣቷ ተነግሯል።
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌላ ባየርቦክ በትናንትናው እለት እንዳስታወቁት፤ ወደ ጂቡቲ ሲጓዝ የነበረው የጀርመን መንግስት አውሮፕላን ያለ እቅድ ሳዑዲ አረቢያ ለማረፍ መገደዱን ገልጸለዋል።
ይህ ሊሆን የቻለውም በኤርትራ የአየር ክልል ላይ ለማለፍ ፍቃድ ባለማግኘቱ እንደሆነም አስታውቀዋል።
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌላ ባየርቦክ በሶስት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለሶስት ቀናት ጉብኝት ለማድረግ በጉዞ ላይ የነበሩ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውም ጂቡቲ እንደነበረች ሮይተርስ ዘግቧል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በሱዳን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ዙሪያ ከኬንያ እና ደቡብ ሱዳን ባልስጣናት ጋር ለምመከርም ቀጠሮ ይዘው ነበር ተብሏል።
አናሌላ ባየርቦክ በመግለጫቸው፤ ያለ እቅድ በሳዑዲ አረቢያ ለማረፍ መገደዳቸው በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ያለውን አለመረጋጋት ያመለክታል ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በመግለጫቸው በጂቡቲ ጉብኝታቸው፤ የአውሮፓ ህብረት የቀይ ባህርን የመርከብ መንገዶችን ከየመን ሁቲ ሚሊሻዎች የሚከላከልበት መንገድ ላይ እየሰራ መሆኑን መልእክት ለማስተላፍ እንደነበረ አስታውቀዋል።
ባለፈው ነሃሴ ላይ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌላ ባየርቦክ ወደ ኢንዶ-ፓሲፊክ ክልል ለማድረግ አቀደው የነበረው የአንድ ሳምንት ጉዞ ከመንግስት አይሮፕላን ላይ ባጋጠሙ ሜካኒካዊ ችግሮች ምክንያት መሰረዙ ይታወሳል።