የጀርመን መንግስት ጉዳዩን እንደሚያጣራ እና እርምጃ እንደሚወስድ በአዲስ አበባ የሀገሪቱ ኤምባሲ ገልጿል
ኢትዮጵያ በጀርመን የሚገኘው ኤምባሲዋ ደህንነት ባለመጠበቁ ቅሬታዋን ገለጸች
ከሰሞኑ በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጊቢ የኢትዮጵያን መንግስት የሚቃወሙ የኦነግ ደጋፊዎች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አውርደው በምትኩ የኦነግን ሰንደቅ ዓለማ ሰቅለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህን በማስመልከት ቅሬታውን በአዲስ አበባ ለሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ ማቅረቡን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ፣ በኢትዮጵያ ከሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ ወኪል አምባሳደር ሄይኮ ኒትሽክ ጋር በሥልክ በነበራቸው ቆይታ በተፈጠረው ድርጊትና በነበረው የጸጥታ መዘናጋት የኢትዮጵያ መንግስት ማዘኑን ገልጸዋል፡፡ ይህንን ድርጊት የፈጸሙት ሰዎች ላይ እርምጃ አለመወሰዱም እንዳሳዘናቸው አምባሳደር ሬድዋን እንደገለጹላቸው የውጭ ጉዳ ሚኒስቴር በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹ የተቃውሞ ሰልፍ የማድረግ መብታቸውን እንደሚደግፍ ፣ ነገር ግን ይህ መሆን ያለበት ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ውጭ መደበኛ ሥራዎች በማይታወኩበት መንገድ መሆን እንዳለበትም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት፡፡
ወኪል አምባሳደሩ በበኩላቸው በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የደረሰው የጸጥታ ችግር ተቀባይነት የሌለውና መደረግ ያልነበረበት መሆኑን ለአምባሳደር ሬድዋን ገልጸውላቸዋል፡፡ የጀርመን መንግስት በኢትዮጵያ ኤማባሲ የተፈጸመውን ጉዳይ በተመለከተ ተጨማሪ ማጣራት እንደሚያደርግ እና ችግሮችን እንደሚቀርፍ ወኪል አማባሳደሩ መናገራቸውም ተገልጿል፡፡
በብሪታኒያ ለንደን ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም በተመሳሳይ መልኩ የሪፐብሊኩ ሰንደቅ ዓላማ መውረዱ የሚታወስ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተም የኢትዮጵያ መንግስት በአዲስ አበባ ለሚገኘው የብሪታኒያ ኤማባሲ ቅሬታውን አሰምቶ ማብራሪያ የጠየቀ ሲሆን ኤምባሲው በተፈጸመው ድርጊት ማዘኑንና ለዚህም ይቅርታ መጠየቁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከቀናት በፊት ገልጿል፡፡