ላለፉት 36 ዓመታት የሀገሪቱን በትረ ስልጣን ጨብጠው የቆዩት ፕሬዝዳንት ዴኒስ ሳሱ ኑጉሶ ምርጫውን እንደሚያሸንፉ ተጠብቋል
በማእከላዊ አፍሪካ የምትገኘውና በዘይት አምራችነቷ የምትታወቀው ኮንጎ ሪፐብሊክ ቀጣይ መሪዋን ለመምረጥ በዛሬው እለት የምርጫ ጣብያዎቿን ለመራጮች ክፍት አድረጋለች፡፡
መራጮች ከጠዋቱ 1፡00 አንስተው ድምፅ በመስጠት ላይ ናቸው፡፡
ሀገሪቱ በከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ውስጥ ብትሆንም በዚህ ምርጫ፤ ላለፉት 36 ዓመታት የሀገሪቱን በትረ ስልጣን ጨብጠው የቆዩት ፕሬዝዳንት ዴኒስ ሳሱ ኑጉሶ እንደሚያሸንፉ ከወዲሁ እየተጠበቀ መሆኑን ነው የሮይተርስ ዘገባ የሚያመለክተው፡፡
ዲፕሎማቶች እና ተንታኞች ግን፤ ከሳሱ ስድስት ተቃዋሚዎች መካከል በአንዳቸው የፕሬዝዳንቱን በትረ ስልጣን ሊነጠቅ እንደሚችል አልያም በ2016 የመጨረሻ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ላይ ያጋጠመው ሁከት ዳግም ሊያጋጥም እንደሚችል ያላቸውን ስጋት አስቀምጠዋል፡፡
የፕሬዝዳንቱ ዋና ተቃዋሚ የሆኑት የቀድሞው ሚኒስትር ጋይ-ብሪስ ፓርፋይት ኮሌላስ በCOVID-19 ምክንያት ሆስፒታል ውስጥ የነበሩ ሲሆን በዛሬው እለት ወደ ፈረንሳይ ሊወሰዱ እንደሚችሉ የኮሌላስ የዘመቻ ዳይሬክተር ለሬዲዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናል ተናግረዋል፡፡
የ77 ዓመት አዛውነቱ ፕሬዝዳንት ሳሱ በ 1979 ወደ ስልጣን የመጡ በ 1992 የኮንጎ የመጀመሪያ የመድብለ ፓርቲ ምርጫን ተሸነፈው ከኃላፊነት የተወገዱ እንዲሁም መሸነፋቸውን ተከትሎ በሀገሪቱ በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት በ 1997 እንደገና የፕሬዝዳንትነቱን በትረ ስልጣን መጨበጥ የቻሉ አፍሪካዊ መሪ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ወደ መሪነት ከተመለሱ በኋላ ህገ-መንግስት ማሻሻያ በማድረግና የስልጣን ገደብን በማራዘም እስካሁን ድረስ ሀገሪቱን በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡