“በሁለት አመታት ውስጥ አጠቃላይ ስርዓቱን ለመቀየር የሚያስችል አስማት ማንም የለውም”
ተሰናባቿ የጀርመን አምባሳደር ስለ ኢትዮጵያ ያሉት ምንድነው?
ከቀናት በፊት የተሰናበቱት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ዋግነር ከታዋቂው የሃገራቸው የዜና አውታር ዶቼ ቬሌ እንግሊዘኛ ጋር ቆይታን አድርገዋል፡፡
በቆይታቸውም ስለ ሃገራዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ የለውጥ ሂደት፣ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ስለገጠመው ህገ መንግስታዊ ቀውስ እንዲሁም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአፍሪካ-አውሮፓ ህብረት (AU-EU relations) ግንኙነት ላይ ስላሳረፈው ተጽዕኖ አውርተዋል፡፡
አምባሳደሯ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)ም አውርተዋል፡፡ በተለይም ሃገራዊ ለውጡን እንዴት እየመሩት እንደሆነና በለውጡ እንደሚያሳኳቸው ከገቧቸው ቃሎች አንጻር አተገባበራቸው ምን እንደሚመስልም የግምገማና ትዝብት አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ይህም ነው ጉዳዩ በተለያዩ የማህበረሰብ ትስስር ገጾች ጎላ ብሎ መነገጋሪያ እንዲሆንም ያደረገው፡፡
አምባሳደር ብሪታ እ.ኤ.አ ከ2017 ጀምሮ ያለፉትን 4 ዓመታት ነው በኢትዮጵያ ያገለገሉት፡፡ ሃገራቸው መቀመጫውን አዲስ አበባ ካደረገው የአፍሪካ ህብረት ጋር ያላትን ግንኙነት ሲከታተሉም ነበር፡፡
በተጨባጭ ምን አሉ?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ስለነበረው ለውጥ በተለይም ስለ ፖለቲካዊው ለውጥ የተጠየቁት አምባሳደሯ “ትልቅ፤ ነገር ግን ያልተጠበቀና እርሳቸውን ጨምሮ ብዙዎችን ያስገረመ ለውጥ” እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ብዙሃኑን አስጨንቆ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም ስልጣን እንዲለቁ አስገድዶ የነበረው ለውጥ ለእያንዳንዱ የመታደስን መንፈስ ያላበሰ እንደነበርም አልሸሸጉም፡፡
ብዙዎችን በተስፋና በአዲስ የለውጥ ስሜት ባፍነከነከው ሃገራዊ ለውጥም ፖለቲካዊ እስረኞች ተለቀዋል፣ ታዋቂው የቃሊቲ [ማዕከላዊ] እስር ቤትም ተዘግቷል፡፡
ጋዜጠኞችም “ከአሁን በኋላ ምንም የሚስፈራ ነገር የለም” ብለውኛልም ይላሉ ዋግነር፡፡
በውጭ ሃገራት ይንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች የለውጡ አካል እንዲሆኑ የቀረበላቸውን ሃገራዊ ጥሪ ተቀብለው ሃገር ቤት ገብተው መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡
በብዙዎች እንደ አሳሪ ተደርገው ይቆጠሩ የነበሩ የበጎ አድራጎትና ማህበራት አዋጆች ተሻሽለው ማኅበራቱ በአንጻራዊነት የተሻለ እንቅስቃሴን እንዲያደርጉ ሆኗል፡፡
ተስፋ ሰጪ ሊባሉ የሚችሉ አዎንታዊ ድባቦች የተስተዋሉበትም ነበረ ለውጡ፡፡
ሆኖም ሁሉም እንደሚሟሉ በማሰብ “ከለውጡ ከሚገባው በላይ ብዙ ተጠብቋል”ይላሉ አምባሳደሯ፡፡ እንዲመጡ የሚታሰቡት ዘርፈ ብዙ አዎንታዊ ለውጦች ምናልባትም የስርዓት ለውጥን ጭምር ሊሹ የሚችሉ እንደሆነና የተባሉትንና ቃል የተገቡትን ሁሉ ለማሟላት ጊዜ እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡
“የተጠበቁት ነገሮች በቀላሉ የተጋነኑ ናቸው”
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጠበቀው እና የሚጠበቀው ነገር ተጋኖ እንደሆነም ዶቼ ቬሌ ይጠይቃል፡፡ ሁለት አስርታትን የዘለቀው የኢትዮ-ኤርትራ ሰላምም ጦርነትም የሌለበት ሻካራ ግንኙነት እንዲያበቃ ማድረጋቸውን ተከትሎ ያገኙት የኖቤል የሰላም ሽልማት የሚጠበቀውን ነገር ይበልጥ አባብሶ አጋነነው ወይ?ም ይላል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ይህንኑ የአንድ መቶ ሚሊዬን እና ከዚያ በላይ ህዝብ ፍላጎት ለመመለስ ይችሉ ይሆን ሲልም ያጠይቃል፡፡
አምባሳደሯም ሲመልሱ “የተጠበቁት ነገሮች በቀላሉ የተጋነኑ” ናቸው፡፡
“ብዙ ነገሮች ተጠብቀዋል [ከጠቅላይ ሚኒስትሩ]፤ አንዳንዶቹ ቃል የገቧቸውና አሁንም እንዲሳኩ የሚፈልጓቸው ናቸው ነገር ግን በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳካት ቀላል አይሆንም” ሲሉም ነው ብሪታ የሚያስቀምጡት፡፡
የሃገር ውስጡን ፖለቲካ ክፍት ያደረጉትን ያህል የኤርትራን ጨምሮ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲውን የተመለከቱ ቤት ስራዎች አሉባቸው፡፡
“በርካታ ነገሮች ቢቀየሩም በሁለት አመታት ውስጥ አጠቃላይ ስርዓቱን ለመቀየር አይቻልም”ያሉት አምባሳደሯ “ይህን ለማድረግ የሚያስችል አስማት” ማንም እንደሌለውም ይናገራሉ፡፡
ኮሮና እና ምርጫ
ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ከተራዘመው ሃገራዊ ምርጫ፣ በምርጫው መራዘም ስለገጠመው ህገመንግስታዊ ቀውስ እና ከቀውሱ ለመላቀቅ የህግ ምሁራን በማድረግ ላይ ስላሉት ጥረት እንዲሁም ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን ጊዜ ተጠይቀውም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ጅምሩ ሃገራዊ ለውጥ እና ምርጫው በኮሮና ምክንያት መስተጓጎላቸው ለኢትዮጵያ አለመታደል ነው ያሉት አምባሳደሯ ሁኔታው አሳዛኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የገጠመውን ሃገራዊ ችግር ለመሻገር ምክር ቤቶችን ጨምሮ በየደረጃው ባሉ የመንግስት አካላት ጥረት እየተደረገ ነው የሚሉም ሲሆን በጥረቱ የመንግስት የስልጣን ዘመን ሊራዘም እንደሚችል ነገር ግን ይህ በህጋዊ እና በፖለቲካዊ መንገዶች ብቻ እንደሚሆን ያስቀምጣሉ፡፡
ሃገራዊ ለውጡና የጀርመን ድጋፍ
ጀርመን ገና ከጅምሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተጀመሩ የለውጥ ተግባራትን እንደምትደግፍ ስለማስታወቋም ተናግረዋል፡፡ የ372 ሚሊዬን ዶላር አዲስ ድጋፍ ለማድረግም ቃል ገብታለች፡፡ ይህንኑ ምጣኔ ሃብታዊና ፖለቲካዊ ድጋፍ ግልጽ ለማድረግም ነበር ፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተን ስቴይንመር ባሳለፍነው ወርሃ ጥር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት፡፡
“ለውጡ እንዲሳካ እንፈልጋለን እንደሚሳካ ተስፋ እንደርጋለን” ብለዋልም፡፡
ሃገራዊ ምርጫው እንዲሳካና ሲደረጉ የነበሩ ዝግጅቶች ሁሉ እንዲሰምሩ 10 ሚሊዬን ዩሮ በመመደብ ከአውሮፓ ህብረትና ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ተቀናጅተው ሲሰሩ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡
“ድጋፋችን ይቀጥላል፣አሁንም ኢትዮጵያ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫን እንድታካሂድ እንፈልጋለን” ሲሉም ብሪታ ተናግረዋል፡፡