"ስካይ ሬንጀር 30" - ጀርመንን ከድሮን ጥቃት የሚጠብቀው መሳሪያ
ተሽከርካሪው ጸረ ድሮን በ3 ሺህ ሜትር ርቀት በጣም ትንሽ ድሮኖችን መምታት የሚችሉ መሳሪያዎችን ይተኩሳል

የጀርመን ጦር 19 "ስካይ ሬንጀር 30" ያዘዘ ሲሆን፥ በቀጣይ ሁለት አመታት ውስጥ ይረከባል ተብሏል
ጀርመን እያደገ የመጣውን የድሮን ጥቃት ለመመከት ተንቀሳቃሽ ጸረ ድሮን ተሽከርካሪ በማምረት ላይ ትገኛለች።
38.5 ቶን የሚመዝነው እና ስምንት ሜትር ርዝመት ያለው ጸረ ድሮን ተሽከርካሪ "ስካይ ሬንጀር 30" የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል።
ተሽከርካሪው በጀርመኑ ኩባንያ ራይሜታይ እየተመረተ እንደሚገኝ ቢልድ ጋዜጣ አስነብቧል።
የሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን ከሰሞኑ ይህንኑ የድሮን ጥቃት አምካኝ ተሽከርካሪ በኪል እኛ ሉቤክ ከተሞች ሲፈተሽ ተመልክተውታል።
"ስካይ ሬንጀር 30" በአንድ ምሽግ ላይ የሚገኙም ሆነ የሚንቀሳቀሱ የጀርመን ጦር ክፍሎችን ከድሮን ጥቃት የሚጠብቅ ጋሽ ነው ተብሏል።
ጸረ ድሮኑ ግቡን እንዲመታ ሁለት የመሳሪያ ስርአቶችን ይጠቀማል።
የመጀመሪያው "ኦርሊኮን" የተባለ ባለ 30 ሚሊሜትር የመድፍ ስርአት ነው። እስከ 3 ሺህ ሜትር ባለው ርቀት መምታት የሚችለው ስርአት አየር ላይ ወደ 150 ፍንጥርጣሪዎች የሚለወጡ መሳሪያዎችን ይተኩሳል።
የመፈንጃው ጊዜ ከኢላማው ርቀት አንጻር ፕሮግራም የሚደረግ ሲሆን ከሚሊሜትር ባታች ያነሱ ፍንጥርጣሪዎች ድሮኑን በስተው መግባት ይችላሉ ተብሏል። ይህም ኢላማ የተደረገውን ድሮን መትቶ ለመጣል ከፍተኛ እድል እንደሚፈጥር ነው ቢልድ ያስነበበው።
ተሽከርካሪውች በፍጥነት ሊተኮሱ የሚችሉ 300 ገደማ ተተኳሾችንም ይዞ ይንቀሳቀሳል።
"ስካይ ሬንጀር 30" ሌላኛው የሚጠቀመው የመሳሪያ ስርአት "አዚሎት" የአየር መቃወሚያ ይሰኛል። ተሽከርካሪው እስከ 6 ሺህ ሜትሮች ድረስ ርቀት የሚምዘገዘጉ አራት ስትሪንገር ሚሳኤሎችን መጫን ይችላል።
በቀጣይም እጅግ በጣም ትንሽ ድሮኖችን ለመምታት የሚውሉ ዘጠኝ "ሲ- ዩኤኤስ" የተሰኙ ሚሳኤሎች ይኖሩታል ተብሏል።
በጀርመኑ ጸረ ድሮን ተሽከርካሪ ውስጥ ሶስት ሰዎች ይኖራሉ፤ አሽከርካሪ፣ ተኳሽ እና አዛዥ።
በተሽከርካሪው ውስጥ የተገጠሙ ሁለት ስክሪኖች በ35 ኪሎሜትር ርቀት ውስጥ አዲስ ነገር መኖሩን በራዳር እንዲመለከቱ ያስችሏቸዋል።
የድሮን ጥቃት ስጋት ሲያጋጥም ተኩስ የሚከፈትበት መንገድም ከቪዲዮ ጨዋታ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ መቆጣጠሪያ መሳሪያዎች (ኮንትሮል ፓኔል) እንደ ስጋቱ አቅጣጫ እየለዋወጡ በመንካት ነው የሚተኩሱት።
የጀርመን ጦር (ቡንዴስቬር) 19 "ስካይ ሬንጀር 30" ጸረ ድሮን ተሽከርካሪዎችን ለመግዛት አዟል። ራይሜታይ ኩባንያ ከ630 ሚሊየን ዩሮ በላይ የሚያወጡትን ተሽከርካሪዎች ከ2027 - 2028 ባለው ጊዜ እንደሚያስረክብም ነው የተነገረው።