ዩክሬን የዓለም ቁጥር አንድ የጦር መሳሪያ ገዥ ስትሆን አሜሪካ በሽያጭ የበላይነቷን አስጠበቀች
በአለም አቀፍ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያለችው ፈረንሳይ ድርሻዋ ከአሜሪካ በአራት እጥፍ ያነሰ ነው

የሩሲያ የጦር መሳሪያ ኤክስፖርት ከአሜሪካ ጋር ሲነጻጸር በ64 በመቶ መቀነሱን የኢንስቲትዩቱ ሪፖርቱ ያሳያል
የስቶኮሆልም ኢንተርናሽናል ፒስ ሪሰርች ኢንስቲትዩት(ኤስአይፒአርአይ) ያጠናው ጥናት እንደሚያሳየው በአለም አቀፍ የጦር መሳሪያ ንግድ ላይ ጉልህ ለውጦች ተስተውለዋል።
ኢንስቲትዩቱ ትናንት ባወጣው ሪፖርት ዩክሬን በዓለም ደረጃ ቁጥር አንድ የጦር መሳሪያ ገዥ ሀገር ስትሆን አሜሪካ ደግሞ በጦር መሳሪያ ኤክፖርት ቀዳሚ በመሆን የበላይነቷን አስጠብቃለች።
አሜሪካ በዋናት የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ የዩክሬን የጦር መሳሪያ ፍላጎት በመጨመሩ የዓለም ቀዳሚ የጦር መሳሪያ ላኪነቷን አጠናክራ ቀጥላለች። የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ እንደሚያመለክተው የአሜሪካ የጦር መሳሪያ ኤክስፖርት ወይም ሽያጭ ስትራተጂካዊ ብቻ ሳይሆን ውስብስብ የሆኑ የጂኦፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ለውጦችን እንዲሁም አለምአቀፍ ጥምረቶች መጠላለፋቸውን የሚያሳይ ነው።
የአሜሪካ የበላይነት
እንደ ሪፖርቱ አሜሪካ ከ2020-2024 ኤክፖርት ያደረገችው የጦር መሳሪያ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ የተባለ የ20 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ የአሜሪካን ዓለምአቀፋዊ የኤክስፖርት ድርሻ ወደ 43 በመቶ ከፍ አድርጎታል።
መጠኑ አሜሪካ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ውስጥ አስመዝባው ከነበረው የ35 በመቶ አማካኝ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ብልጫ አለው።
አሜሪካ የቅርብ ተፎካካሪዋን ፈረንሳይን በከፍተኛ ልዩነት በመብለጥ ቀደሚ መሆኗ አሜሪካ በጦር መሳሪያ ንግድ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣቷን የሚያሳይ ነው ተብሏል። በአለም አቀፍ የጦር መሳሪያ ኤክስፖርት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያለችው ፈረንሳይ የኤክስፖርት ድርሻዋ ከአሜሪካ በአራት እጥፍ ያነሰ ነው።
የአሜሪካ የ2024 የጦር መሳሪያ ሽያጭ 29 በመቶ በማደግ በታሪክ ከፍተኛ የተባለ 318.7 ቢሊዮን ዶላር ሆኖ ተመዝግቧል። የአጋሮች ለዩከሬን ብዙ ቁጥር ያለው የጦር መሳሪያ ከላኩ በኋላ የመሳሪያ ክምችታቸውን ለመሙላት ያሳዩት ግዴለሽነት ለአሜሪካ የጦር መሳሪያ ሽያጭ መጨመር እንደምክንያት ይጠቀሳል። ይህ ለአሜሪካ የጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች ወርቃማ እድል ተፈጥሮላቸዋል።
ቀዳሚ የጦር መሳሪያ ገዥ ሀገር
ዩክሬን በጦርነት ምክንያት ከ2020-2024 የአለም ቁጥር አንድ የጦር መሳሪያ ገዥ ሀገር ሆናለች። ከ2015-2019 ባለው ጊዜ ውስጥ የዩክሬን የጦር መሳሪያ ግዥ ከ2015-2019 ካለው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር መቶ በመቶ አድጓል።
የሩሲያ ማሽቆልቆል
ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ የሩሲያ የጦር መሳሪያ ኤክስፖርት ከአሜሪካ ጋር ሲነጻጸር በ64 በመቶ መቀነሱን የኢንስቲትዩቱ ሪፖርቱ ያሳያል። እንደሪፖርቱ ከሆነ የሩሲያ ጦር መሳሪያ ሽያጭ መቀነስ የጀመረው ከዩክሬን ጦርነት በፊት ጀምሮ ነው። ለጦር መሳሪያ አቅርቦቶቻቸው በሞስኮ ላይ ጥገኛ የነበሩት ህንድና ቻይና ጥገኝነታቸውን መቀነሳቸው ለሩሲያ ጦር መሳሪያ ሽያጭ መቀነስ አንደኛው ምክንያት እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
ህንድ የጦር መሳሪያ የምትገዛባቸውን ምንጮች ስታሰፋ ቻይና በአንጻሩ እያደገ ባለው የሀገር ውስጥ የጦር መሳሪያ ኢንዱስትሪዋ ላይ ተማምናለች።