የጀርመኑ ነዳጅ አከፋፋይ ድርጅት ዩኒፐር ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ መክሰሩን አስታወቀ
ኩባንያው ኪሳራ ያስመዘገበው በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት መሆኑን አስታውቋል
ወደ ጀርመን የሚገባው የሩሲያ ነዳጅ በዚሁ ከቀጠለ ኪሳራው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችልም ኩባንያው አስታውቋል
የጀርመኑ ነዳጅ አከፋፋይ ድርጅት ዩኒፐር ከ12 ቢሊዮን በላይ ዶላር መክሰሩን አስታወቀ፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ከገቡ 175ኛ ቀናቸውን ላይ ይገኛሉ፡፡
ይህ ጦርነት ጉዳቱ ከሁለቱ ጦርነት ባለፈ የዓለምን ኢኮኖሚ እና ዲፕሎማሲ በማፋለስ ላይ ሲሆን በአውሮፓ ሀገራት ላይ ጉዳቱ እየጨመረ ይገኛል፡፡
40 በመቶ አውሮፓዊያን የነዳጅ ፍላጎታቸውን ከሩሲያ ያገኙ የነበረ ሲሆን ጦርነቱን ተከትሎ አውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ በሩሲያ ንግድ ላይ ማዕቀብ መጣላቸውን ተከትሎ የነዳጅ እጥረቱ በየዕለቱ እየጨመረ ይገኛል፡፡
የአውሮፓ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚዋ ጀርመን በሩሲያ ነዳጅ ላይ ጥገኛ ከሆኑ ሀገራት መካከል ዋነኛዋ ሀገር ስትሆን የነዳጅ እጥረቱ እንደጎዳት ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከሩሲያው የነዳጅ አቅራቢ ጋዝፕሮም ነዳጅ በመሸመት ለጀርመኖች የሚያከፋፍለው ዩኒፐር የተሰኘው ኩባንያ በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራ ማስተናገዱን አስታውቋል፡፡
ዩኒፐር ኩባንያ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር እንደከሰረ የገለጸ ሲሆን ከሩሲያ የሚፈለገውን ነዳጅ እያስገባ አለመሆኑ እንዳሳሰበውም ገልጿል፡፡ድርጅቱ አሁን ያጣውን ትርፍ እስከ 2024 ዓመት ድረስ መመለስ እንደማይችል የገለጸው ይህ ተቋም የጀርመን መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስቧል፡፡
ዩኒፐር ከዚህ በፊት በቂ መጠን ያለው ነዳጅ ከሩሲያ በርካሽ ዋጋ ያገኝ እንደነበር ገልጾ አሁን ላይ የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ ማዕቀብ መጣሉን ተከትሎ በውድ ዋጋ ከሌሎች ሀገራት እየገዛ መሆኑንም አስታውቋል፡፡