ጀርመን የቦምብ መጠለያዎችን በስፋት እያዘጋጀች መሆኑ ተሰማ
የዩክሬን እና ሩስያ ጦርነት ውጥረት እየተጋጋለ መሆኑን ተከትሎ የአውሮፓ ሀገራት ግጭቱ በራቸውን ለያንኳኳ እንደሚችል ሰግተዋል
በርሊን በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ 579 የቦንብ መጠለያዎች አሏት
የአውሮፓዋ ሀገር ጀርመን የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ውጥረትን ተከትሎ ለጦርነት ዝግጅት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
ሀገሪቱ በጦርነት እና በአደጋ ጊዜ ዜጎች ከጥቃት ራሳቸውን ሊከላከሉባቸው የሚችሉ የቦምብ መጠለያዎችን (ምሽጎችን) በመዘጋጀት ላይ እንደምትገኝ ነው የተነገረው፡፡
በዋናነት የባቡር ጣብያዎችን ለቦንብ መጠለያነት ለማዋል ዝግጅት እያደረገች የምትገኝው በርሊን ዜጎች የመኪና ማቆሚያዎቻቸውን እና በመኖርያ ቤቶቻቸው ስር የሚገኙ ምድር ቤቶችን ለአደጋ ጊዜ መጠለያነት እንዲያዘጋጁ አዛለች፡፡
የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሩሲያ ጋር ግጭት ውስጥ የሚገባ ከሆነ ለዜጎች ድንገተኛ መጠለያ የሚሆኑ የተጠናከረ መጠለያዎችን ዝርዝር እያዘጋጀ መሆኑን ገልጿል።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ እንዳብራሩት ዝርዝሩ የመሬት ውስጥ ባቡር ጣቢያዎች ፣ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች ፣የመንግስት ህንጻዎች እና የግል ንብረቶችን ያካትታል።
መንግስት ባዘጋጀው እቅድ መሰረት ሰዎች የስልክ መተግበርያዎችን በመጠቀም የድንገተኛ አደጋ መጠለያዎች የት እንደሚያገኙ የሚጠቁሙ ዲጂታል መመሪያዎችን በማዘጋጀት ላይ ነው፡፡
ዕቅዱ ግዙፍ እና ጊዜ የሚወስድ መሆኑን ተከትሎ ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ይፋ ያላደረገው መንግስት የሀገሪቱ የህዝብ ጥበቃ እና የአደጋ ጊዜ ቢሮ እቅዱን በዋናነት እንደሚያስፈጽም አስታውቋል፡፡
የናዚ መሪ አዶልፍ ሂትለር ራሱን ከማጥፋቱ በፊት የበርሊን ጦርነትን ሲመራበት የነበረውን ጨምሮ ሀገሪቱ በምሽጎች እና በቦንብ መጠለያዎች ግንባታ ትታወቃለች፡፡
በሁለተኛው የአለም ጦርነት እና በቀዝቃዛው የአለም ጦርነት ወቅት ከ2ሺ በላይ መጠለያዎች የነበሯት ጀርመን ከጦርነቶቹ በኋላ በርካቶቹን በማፍረስ በአሁኑ ወቅት 579 የሚጠጉ የአደጋ ጊዜ መጠለያዎች ብቻ ቀርተዋታል፡፡
እነዚህ መጠለያዎች 84 ሚሊየን ህዝብ በሚገኝባት ሀገር ማስጠለል የሚችሉት 480 ሺህ ዜጎችን ብቻ ነው፡፡
የዩክሬን ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሞስኮ ሌሎች የኔቶ አባል ሀገራትን ኢላማ ልታደርግ እንደምትችል ከፍተኛ የደህንነት ስጋት አለ፡፡
ይህ ስጋት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆባይደን ኪቭ በሞስኮ የሚገኙ ኢላማዎችን በምዕራባውያን ሰራሽ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎች ጥቃት እንድትፈጽም ፈቃድ መስጠታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ እያየለ ይገኛል፡፡
ከሰሞኑ ስዊድን እና ኖርዌን ጨምሮ ሌሎች የኖርዲክ ሀገራት ዜጎቻቸው ለጦርነት እንዲዘጋጁ በማስጠንቀቅ ላይ እንደሚገኙ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ሩሲያ በቅርቡ በአውሮፓ ሀገራት እና የአሜሪ የባህር ጠረፎች ላይ በደቂቃ መድረስ የሚችል ኦሬሽኒክ የተባለ አዲስ ሚሳኤል ጥቅም ላይ አውላለች፡፡
ባሳለፍነው ጥቅምት ወር የጀርመን የስለላ ሃላፊዎች ሩሲያ እ.ኤ.አ. በ2030 በኔቶ አባል ሀገራት ላይ ጥቃት ልትሰነዝር እንደምትችል ማስጠንቀቃቸውን ዘ ጋርዲን ዘግቧል፡፡