ጀርመን ከ500 ሺህ በላይ የሰራተኞች እጥረት እንዳለባት አስታወቀች
የጤና እና ግንባታ ሙያ መስኮች ያለው እጥረት ስር የሰደደ ነው ተብሏል
በጀርመን እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸው ዜጎች ቁጥር መጨመር የሰራተኛ እጥረቱን እንዳባበሰው ተገልጿል
ጀርመን ከ500 ሺህ በላይ የሰራተኞች እጥረት እንዳለባት አስታወቀች፡፡
በአውሮፓ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ጀርመን የሰለጠነ የሰራተኞች እጥረቱ እንደተባባሰ ተገልጿል፡፡
አሁን ላይ እድሜያቸው የገፉ ጀርመናዊያን ቁጥር እየጨመረ ሲሆን ይህ ማህበረሰብ በ2030 ከጠቅላላው ህዝብ ውስጥ ያለው ድርሻ ወደ 29 በመቶ ከፍ እንደሚል ተገልጿል፡፡
እንደ ጀርመን ድምጽ ዶቸቪሌ ዘገባ ከሆነ በጀርመን የጤና ባለሙያዎች እጥረት አንገብጋቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
በተለይም በስነ ልቦና እና ጥርስ ህክምና ዘርፍ ከፍተኛ የሚባል እጥረት አጋጥሟል የተባለ ሲሆን በተጠቀሲት መስኮች 47 ሺህ የስራ መደቦች ክፍት ናቸው ተብሏል፡፡
ጀርመን የሰራተኛ ዕጥረቷን ለመፍታት በሚል ወደ ሀገሯ እንዲገቡ የፈቀደችላቸው ሀገራት እነማን ናቸው?
ሮበርት ኮች ኢንስቲትዩት እንዳጠናው ጥናት ከሆነ እድሜያቸው ለጡረታ የደረሱ ጀርመናዊያን ቁጥር እየጨመረ ሲሆን ይህ ደግሞ የሰው ሀይል እጥረቱን እንዳባበሰው ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ ጀርመን በተያዘው 2024 ዓመት ብቻ 530 ሺህ የሰለጠኑ ሰራተኞች የሚያስፈልጋት ሲሆን እጥረት ከጤና ቀጥሎ የግንባታ ባለሙያዎች ከፍተኛ እጥረት የጣየበት መስክ ነው ተብሏል፡፡
ጀርመን የገጠማትን የሰለጠነ የሰው ሀይል ችግር ለመፍታት ከስራ እና ዜግነት ጋር የተያያዙ ፖሊሲዎቿን በመከለስ ላይ እንደምትገኝ ከዚህ በፊት መግለጿ አይዘነጋም፡፡