በአውሮፓ ዋንጫ ጀርመን እና ስዊዘርላንድ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቀሉ
የ2021 ሻምፒዮኗ ጣሊያን በ2006 የአለም ዋንጫን ባነሳችበት ስታዲየም ተሸንፋ ከ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ተሰናብታለች
ዛሬ ምሽት እንግሊዝ ከስሎቫኪያ፤ ስፔን ከጆርጂያ የሚያደርጉት የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ይጠበቃል
የአውሮፓ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ትናንት ምሽት ሲጀመሩ አስተናጋጇ ጀርመን ወደ ሩብ ፍጻሜው መግባቷን አረጋግጣለች።
በዶርትሙንድ ዌስትፋለን ስታዲየም ዴንማርክን የገጠመችው ጀርመን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፋለች።
የአርሰናሉ ካይ ሃቨርትዝ እና የባየር ሙኒኩ ጀማል ሙሴይላ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።
በውድድሩ እስካሁን 10 ጎሎችን ያስቆጠረው የጀርመን ብሄራዊ ቡድን በርካታ ጎሎችን በማግባት እየመራ ይገኛል።
የትናንት ምሽቱን ድል ተከትሎም በሩብ ፍጻሜው ዛሬ ምሽት ከሚጫወቱት ስፔንና ጆርጂያ አሸናፊ ጋር የፊታችን አርብ ትጫወታለች።
በሌላ በኩል በበርሊን ኦሎምፒክ ስታዲየም ስዊዘርላንድን የገጠመችው ጣሊያን ከ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ተሰናብታለች።
የሉቺያኖ ስፓሌቲ ቡድን 2 ለ 0 ተሸንፎ ነው ከውድድሩ የተሰናበተው።
አዙሪዎቹ ከሶስት አመት በፊት በዌምብሌይ እንግሊዝን አሸንፈው ሶስተኛ የአውሮፓ ዋንጫቸውን ማንሳታቸው አይዘነጋም።
በፈረንጆቹ 2006 ፈረንሳይን በማሸነፍ አራተኛ የአለም ዋንጫቸውን ባነሱበት በርሊን ኦሎምፒክ ስታዲየም ትናንት ምሽት ያሳዩት አቋም ግን እጅግ ደካማ ነበር።
ጣሊያንን አሸንፋ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለችው ስዊዘርላንድ ቅዳሜ ከእንግሊዝና ስሎቫኪያ አሸናፊ ጋር ትጫወታለች።
የጋሬዝ ሳውዝጌት ቡድን ምሽት 1 ስአት ላይ ስሎቫኪያን በቨልቲንስ አሬና ይገጥማል።
የአውሮፓ ዋንጫን ሶስት ጊዜ በማንሳት ከጀርመን የምትስተካከለው ስፔን ምሽት 4 ስአት ላይ ከጆርጂያ ጋር የምታደርገው ጨዋታም ይጠበቃል።