60 ሚሊዮን ዶላር የሚያሸልመው የኢ-ስፖርት ዓለም ዋንጫ ከአራት ቀናት በኋላ ይጀመራል
ውድድሩ በሳውዲ አረቢያ መዲና ሪያድ ከሀምሌ 26 ጀምሮ ለ52 ቀናት ይካሄዳል
በውድድሩ ላይ ከ1 ሺህ 500 በላይ ተጫዋቾች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል
60 ሚሊዮን ዶላር የሚያሸልመው የኢ-ስፖርት ዓለም ዋንጫ
በነዳጅ ሀብቷ የበለጸገችው ሳውዲ አረቢያ ከአንድ ዓመት በፊት ኢ-ስፖርት ያለም ዋንጫ የሚል አዲ የስፖርት ውድድር እንደምታዘጋጅ አስታውቃ ነበር፡፡
በየዓመቱ ክረምት ወር ላይ ይካሄዳል የተባለው ይህ ውድድር ቴክኖሎጂዎችን መሰረት ያደረጉ የዓለም ዋንጫ ውድድሮችን ያካተተ ነው፡፡
ሀገሪቱ ለዋንጫ አሸናፊዎች በአጠቃላይ 60 ሚሊዮን ዶላር ያዘጋጀች ሲሆን ውድድሩ ከሰኔ 26 ቀን እስከ ነሀሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በሪያድ ይካሄዳል፡፡
እንደ ሳውዲ አረቢያ ዜና አገልግሎት ዘገባ ከሆነ በዚህ ውድድር ላይ በ21 የውድድር አይነቶች 30 ክለቦችን የወከሉ 1ሺህ 500 ተጫዋቾች ሳተፋሉ፡፡
ለጨዋታ አሸናፊዎች 33 ሚሊዮን ዶላር፣ በየውድድሩ ኮኮብ ለሆኑ ተጫዋቾች 1 ሚሊዮን ዶላር፣ ወደ ቀጣይ ዙር ለሚያልፉ 7 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለሌሎች የማጣሪያ ጨዋታ አሸናፊዎች 20 ሚሊዮን ዶላር ይሸለማሉም ተብሏል፡፡
100 ሺህ ዶላር የሚያሸልመው አዲሱ የፊፋ የእግር ኳስ ውድድር ምንድን ነው?
በውድድሩ ላይ በስፖርት ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት፣ የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጆች እና ፈጣሪዎች በውድድሩ ላይ ከሚሳተፉት መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
አዲዳስ፣ ሶኒ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ታዋቂ የንግድ ኩባንያዎች የውድድሩ ስፖንሰሮች እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
ሳውዲ አረቢያ ይህን ውድድር ይፋ ያደረገችው ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ ጎብኚዎችን ለመሳብ፣ የ2029 የእስያ ዓመታዊ ውድድሮችን ለማዘጋጀት እንዲሁም የ2034 ፊፋ ዓለም ዋንጫ እና ኦሎምፒክ ውድድሮችን ለማስተናገድ በሚል ነው፡፡
እንዲሁም የሳውዲ አረቢያ እግር ኳስን ጨምሮ የስፖርት ባህልን ለማሳደግ እንደሆነ የሀገሪቱ መንግስት አስታውቋል፡፡
ሀገሪቱ ይህን ውድድር በየዓመቱ የማዘጋጀት እቅድ ያላት ሲሆን በ2030 ከውድድሩ የምታገኘውን ዓመታዊ ገቢ ከ13 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማድረስ እና ለ39 ሺህ ዜጎች የስራ እድል የመፍጠር ግብንም አስቀምጣለች፡፡