በድንቃ ድንቅ መዝገብ ለመስፈር ለ127 ስአታት የዘፈነችው ጋናዊት
ጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋቿ አፉዋ አሳንቴዋ በ2012 የተያዘውን ክብረወሰን ከ20 ስአት በላይ አሻሽላለች
አሳንቴዋ በእንቅልፍ ማጣትና የአዕምሮ መረበሽ ምክንያት ዘፈኗን ማቋረጧ ተገልጿል
ከአምስት ቀናት በላይ ያለማቋረጥ የዘፈነችው ጋናዊት በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ስሟን ለማስፈር ተቃርባለች።
ጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋቿ አፉዋ አሳንቴዋ ለ126 ስአት ከ52 ደቂቃዎች በመዝፈን ነው በ2012 የተያዘውን ክብረወሰን ለማሻሻል የሞከረችው።
ህንዳዊቷ አቀንቃኝ ሱኒል ዋግማሬ ለ105 ስአታት ያለማቋረጥ በመዝፈን ክብረወሰን መያዟ ይታወሳል።
የማያልቅ ጉልበት፣ ጽናትና ትኩረትን የሚሻውን ረጅም ስአት በማቀንቀን በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ የመስፈር በርካቶች ቢሞክሩትም ለእሰርት አመታት የህንዳዊቷ አቀንቃኝ ክብረወሰን ሳይሰበር ቆይቷል።
በፈረንጆቹ ገና ዋዜማ መዝፈን የጀመረችው አሳንቴዋ በህክምና ባለሙያዎች ትዕዛዝ መዝፈን እንድታቆም ቢደረግም በ2012 ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን በ20 ስአት ማሻሻሏ ተነግሯል።
አሳንቴዋ የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ማረጋገጫ እንዲሰጣት እየተጠባበቀች ነው ተብሏል።
ጋናዊቷ ጋዜጠኛ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ለ126 ስአታት ከ52 ደቂቃዎች ስታቀነቅን በየእያንዳንዱ ስአት የ5 ደቂቃ እረፍት አድርጋለች።
ይሁን ኣንጂ ከፍተኛ የእንቅልፍ መዛባት እና የአዕምሮ መጨናነቅ ስላጋጠማት መዝፈኗን እንድታቋርጥ አድርገናል ብለዋል ሲከታተሏት የቆዩ የህክምና ባለሙያዎች።