ከአለማችን ህዝብ 3 ነጥብ 8 በመቶው ተጨማሪ አንድ ጥርስ (33) እንዳለው ይነገራል
የ26 አመቷ ህንዳዊት ወጣት በርካታ ጥርሶች ያሏት እንስት ተብላ በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ስሟ ሰፍሯል።
ካልፓና ባላን የተባለችው እንስት ከመደበኛው የሰው ልጅ ጥርስ ብዛት በስድስት የሚልቅ 38 ጥርሶች እንዳሏት ተነገሯል።
የአንድ ልጅ እናቷ ካልፓና በታችኛው መንጋጋዋ ተጨማሪ አራት ጥርሶች እና በላይኛው መንጋጋዋ ሁለት ጥርሶች አሏት ብሏል የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ በድረገጹ።
ተጨማሪ ጥርሶቹ በልጅነቷ በተለያየ ጊዜ መውጣታቸውን የምታወሳው ካልፓና፥ ምግብ ስትመገብ ከመቸገሯ ውጭ ሌላ ችግር እንዳልገጠማት ትናገራለች።
በመደበኛ ጥርሶቿ ጎን ተደርበው የበቀሉትን ጥርሶች ለማስነቀል ያደረገችው ጥረትም ለመንቀል ስለሚያቸግሩ በደንብ ይደጉ በሚል የሀኪሞች ምክር ሳይሳካ መቅረቱን ነው የምትገልጸው።
የሀኪሞቹ ምክር ግን የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ስሟን እንድታሰፍር አግዟታል።
በወንዶች 41 ጥርሶች ያሉት ካናዳዊው ኢቫኖ ሜሎኒ ክብረወሰኑን እንደያዘ ነው።
ከ32 ጥርሶች በላይ ማብቀል በህክምናው ሃይፐርዶንሺያ ወይም ፖሊዶንሺያ የሚል መጠሪያ የሚሰጠው ሲሆን፥ በምን ምክንያት ሊከሰት እንደሚችል ግን እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ከአለማችን ህዝብ 3 ነጥብ 8 በመቶው ከመደበኛው 32 ተጨማሪ አንድ ጥርስ እንዳለው ጥናቶች ያሳያሉ።