6 መኪናዎችን በጥርሱ የጎተተው ዩክሬናዊ አዲስ ክብረወሰን አስመዘገበ
ዲሚትሮ ህሩንስኪ ከነሾፌሮቻቸው የጎተታቸው ተሽከርካሪዎች አጠቃላይ ክብደት 7 ሺህ 604 ኪሎግራም ነው
ዩክሬናዊው ከ32 ሺህ ኪሎግራም በላይ የሚመዝን ተሽከርካሪን በአንገቱ በመጎተትም በድንቃድንቅ መዝገብ ሰፍሯል
የ34 አመቱ ዩክሬናዊ ዲሚትሮ ህሩንስኪ ሁለት አዳዲስ ክብረወሰኖችን ማስመዝገቡን የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ በድረገጹ አስታውቋል።
ህሩንስኪ ስድስት ተሽከርካሪዎችን በጥርሱ በመጎተት ከዚህ ቀደም ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን ማሻሻል ችሏል።
ግለሰቡ መኪኖቹን ብቻ ሳይሆን በውስጣቸው የነበሩ ሾፌሮችን ጭምር ነው በጥርሱ የጎተተው።
አጠቃላይ የተሽከርካሪዎቹ እና ሾፌሮቹ ክብደትም 7 ሺህ 604 ኪሎግራም እንደነበር ነው የተገለጸው።
አውስትራሊያዊው ትሮይ ኮንሊ ማግኑሰን በ2021 አምስት ተሽከርካሪዎችን በጥርሱ በመጎተት ክብረወሰኑን ይዞ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
ዩክሬናዊው ዲሚትሮ ህሩንስኪ ይህን ክብረወሰን በስድስት ተሽከርካሪዎች ከመስበሩም ባሻገር በ30 ሜትር ውስጥ በፍጥነት ተሽከርካሪን በጥርሱ በመጎተት ሌላ ክብረወሰን ይዟል።
ህሩንስኪ 1 ሺህ 40 ኪሎግራም የምትመዝን (በውስጧ ከያዘችው ሾፌር ጋር 1 ሺህ 100 ኪሎግራም) ታክሲን 30 ሜትር ለመጎተት የወሰደበት 15 ነጥብ 63 ስከንድ ነው።
በዚህም በሶሪያዊው ሳሌህ ያዛን በ2022 ተይዞ የነበረውን (18 ነጥብ 13 ሰከንድ) በማሻሽል አዲስ ክብረወሰን አስመዝግቧል።
በ2022 32 ሺህ 500 ኪሎግራም የሚመዝን ግዙፍ ተሽከርካሪን በአንገቱ በመጎተት ስሙን በድንቃድንቅ መዝገብ ያሰፈረው ዩክሬናዊ በቀጣይም የራሱን ሪከርድ መስበር እንደሚፈልግ ገልጿል።
ያስመዘገበውን ክብረወሰንም ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ጦርነት “ከአንድ አመት በላይ አይበገሬነቷን ላሳየችው” ሀገሩ ዩክሬን መታሰቢያ እንዲሆንለትም ጠይቋል።