የጋና ፕሬዝዳንት አፍሪካውያን ዓለም አቀፍ ክብርን ለማግኘት ምዕራባውያንን መለመን ማቆም አለባቸው አሉ
በዋሽንግተን አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው የአሜሪካ-አፍሪካ ጉባኤ ወደ 50 የሚጠጉ የአፍሪካ መሪዎች እየተሳተፉ ነው
ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ-አዶ መለመን ካቆምን ዓለም ለአፍሪካ አህጉር ያለው አመለካከት ይቀየራል ብለዋል
የጋና ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ-አዶ የአፍሪካ ሀገራት ዓለም አቀፍ ክብርን ለማግኘት ምዕራባውያንን መለመን ማቆም አለባቸው አሉ፡፡
ናና አኩፎ-አዶ ይህን ያሉት በዋሽንግተን እየተካሄደ ባለው የአሜሪካ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡
አፍሪካውያን ምዕራባውያንን መለመን ካቆሙ ዓለም ለአፍሪካ አህጉር ያለው አመለካከት እንደሚቀየርም የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ "ለማኝ መሆናችንን ካቆምን እና የአፍሪካን ገንዘብ በአህጉሪቱ ውስጥ ፈሰስ ካደረግን አፍሪካ ከማንም ክብር የምትጠይቅ አህጉር አትሆንም፤ የሚገባንን ክብር እናገኛለን ።
አፍሪካን መሆን እንዳለባት ካበለጸግናት ክብር ይከተላል"ም ብለዋል፡፡
በጋራ ለማደግ በአፍሪካውያን መካከል የላቀ ትብብር እንዲኖርም አሳስበዋል ፕሬዝዳንቱ።
"አፍሪካውያን በሀገሮቻቸው ከሚኖሩበት በላቀ በሌሎች አህጉራት ላይ አይበገሬነትን አሳይተዋል፡፡
ለውጭው ዓለም እንደ ናይጄሪያዊ፣ ጋናዊ፣ ወይም ኬንያዊ ሳይሆን የጋራ ማንነታችንን፣ አፍሪካዊነትን መዘንጋት የለብንም። እንደ አህጉሪቷ ዜጎች እጣ ፈንታችን እርስ በርስ የተሳሰረ ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አህጉሪቱ ክህሎት እና የሰው ሃይል ቢኖራትም የተቀናጀ የፖለቲካ ፍላጎትና ቀናነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የናና አኩፎ-አዶ ንግግር ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በምዕራብ አፍሪካ ታይቶ የማይታወቅ የኢኮኖሚ ውድቀት የገጠማትን ምእራብ አፍሩካዊቷ ሀገር ጋና ያላትን ቀውስ ለማቃለል ያስችላት ዘንድ የ 3 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠት በተስማማበት ቀን የተደረገ ነው።
ቀድሞውንም በከፍተኛ ዕዳ የተሸከመችው ጋና ከ 40 በመቶ በላይ የዋጋ ግሽበት እና የመገበያያ ገንዘብ ዋጋ ውድቀት ገጥሟታል፡፡
ቀውሱ በተለይም የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲባባስ አድርጎታልም ነው የተባለው፡፡
በፕሬዝዳንት ባይደን አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው ቁልፍ ጉባኤ ወደ 50 የሚጠጉ የአፍሪካ መሪዎች እና ልዑካን በዋሽንግተን ዲሲ ይገኛሉ።
ጉባኤው በአፍሪካ እየጨመረ የመጣውን የቻይና እና የሩሲያ ተጽእኖ እንደሚያስጨንቃት የሚነገርላት ሀገረ አሜሪካ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት የምታጠናክረበትና የምታድስበት ነው ተብሏል፡፡