ሩሲያዊው 'የሞት ነጋዴ' ቪክቶር ቡት የምዕራቡ ዓለም ሩሲያን ማጥፋት ይፈልጋል አለ
የ55 አመቱ አዛውንት በአንዳንድ የምድራችን ደም አፋሳሽ ግጭቶች አማጺዎችን በማስታጠቅ ይከሰሳል
ቪክተቶር ቡት በእስር ላይ አብረውት ከነበሩት መካከል ምንም ዓይነት "ሩሶፎብያ" እንዳላጋጠመው ተናግሯል
ከአሜሪካዊቷ የቅርጫት ኳስ ኮከብ ብሪትኒ ግሪነር ጋር በተደረገ የእስረኛ ልውውጥ ከእስር የተፈታው ሩሲያዊ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪ ቪክቶር ቡት የምዕራቡ ዓለም ሩሲያን ማጥፋት ይፈልጋል አለ፡፡
“ምዕራቡ ዓለም በ1990 ሶቭየት ህብረት መበታተን በጀመረችበት ወቅት እኛን አላስጨረሱንም ብለው ያምናሉ...እኛን እንደገና ለማጥፋት እና ሩሲያን ሊከፋፍሉን እንደሚችሉ ያስባሉ” ሲልም ነው ቪክቶር ቡት ቀደም ሲል ሩሲያ ቱዴይ ተብሎ ለሚጠራውና በመንግስት ስር ለሚተዳደረው ቻናል የተናገረው፡፡
“የሞት ነጋዴ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ቡት የሩሲያ ዜግነት ያለው ሲሆን እጅግ አደገኛ የተባለ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ነጋዴና አዘዋዋሪ ነው።
የ55 አመቱ አዛውንት በአንዳንድ የምድራችን ደም አፋሳሽ ግጭቶች አማጺዎችን በማስታጠቅ ይከሰሳል።
ሆሊውድ በርሱ ህይወት ላይ ‘ሎርድ ኦፍ ዎር’ የተሰኘ ፊልም እስከመስራት ደርሷል።
25 ዓመታት ጽኑ እስር ተፈርዶበት የነበረው ቪክቶር ቡት ላለፉት 12 ዓመታት በአሜሪካ እስር ቤት ነበር።
ቡት በአሜሪካና ሩሲያ ስምምነት መሰረት ከተለቀቀ በኋላ የምዕራቡ ዓለም ለሩሲያ ያለውን መጥፎ አመለካከትና ምኞች ቢገልጽም፤ በእስር ቆይታው በማንነቱ ያጋጠመው ነበር እንደሌለ ከሩሲያ ቱዴይ ጋር በነበረው በቃለ ምልልስ ተናግረዋል፡፡
በእስር ላይ ከሚገኙት እስረኞች መካከል ምንም ዓይነት " ሩሶፎብያ" እንዳላጋጠመው የገለጸው ቪክቶር ቡት፤ , "በመሰረቱ ሁሉም እስረኛማለት ይቻላል … ለሩሲያ የሆነ ዓይነት ርህራሄ ነበራቸው" ሲል በአሜሪካ መንግስት እጅ ሆኖ ስላሳለፋቸው የእስር ላይ አመታት አስታውሷል፡፡
በትናንትናው እለት የተደረገው የእስረኛ ልውውጡ እንዲሰምር የሳኡዲው ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማንና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ፕሬዝዳንት መሐመድ ቢን ዛይድ አል ነህያን ሁነኛ ሚና መጫወታቸው ይገለጻል፡፡