ጋናዊው አጥቂ ራፋኤል ድዋሜና በጨዋታ መሀል ህይወቱ አለፈ
የቀድሞው ሬድቡል ሳልዝበርግ ክለብ ተጫዋች የነበረው ራፋኤል ለአልባኒያው ኢግናቲያ ክለብ እየተጫወተ ነበር
ተጫዋቹ ከዚህ በፊት ከልብ ህመም ጋር በተያያዘ እግር ኳስ መጫወት እንዲያቆም ተነግሮት ነበር ተብሏል
ጋናዊው አጥቂ ራፋኤል ድዋሜና በጨዋታ መሀል ህይወቱ አለፈ።
የ28 ዓመቱ ጋናዊው ራፋኤል ድዌሜና እግር ኳስ እየተጫወተ እያለ ህይወቱ ማለፉ ተገልጿል።
ተጫዋቹ ለአልባኒያ ሱፐርሊግ ተሳታፊው ኢግናቲያ ክለብ ከፓርቲዛኒ ጋር እየተጫወተ እያለ ተዝለፍልፎ መውደቁን ዶቸቪሌ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ ተጫዋቹ በትናንትናው ዕለት የክለብ ጨዋታውን እያደረገ እያለ በ23ኛው ደቂቃ ላይ ከወደቀ በኋላ ህይወቱ አልፏል ተብሏል።
የአልባኒያ ሊግን በስምንት ጎሎች በኮኮብ ግብ አግቢነት እየመራ የነበረው ይህ ጋናዊ አጥቂ በአጨዋወቱ አድናቆትን ያገኘ ነበር።
የተጨዋቹን ህይወት ማለፍ ተከትሎ የአልባኒያ ሱፐርሊግ እግር ኳስ ውድድር ለጊዜው የተቋረጠ ሲሆን ድርጊቱ ብዙዎችን አሳዝኗል ተብሏል።
ተጫዋቹ ከዚህ በፊትም የልብ ህመም እንዳለበት ያተገለጸ ሲሆን ከኦስትሪያው ሬድቡል ሳልዝበርግ ወደ እንግሊዙ ብራይተን በ11 ሚሊዮን ዩሮ ሊዘዋወር ከጫፍ ከደረሰ በኋላ ከልብ ህመም ጋር በተያያዘ በህክምና ምርመራ ምክንያት ዝውውሩ ውድቅ ተደርጎ እንደነበር ተገልጿል።
ይህን ተከትሎም ተጫዋቹ እግር ኳስ መጫወት ካላቆመ ለህይወቱ አስጊ እንደሚሆን የተነገረው ቢሆንም ተጫዋቹ ለእግር ኳስ ባለው ፍቅር ምክንያት መጫወቱን ቀጥሏል ተብሏል።
ለስዊዘርላንዱ ዙሪክ እግር ኳስ ክለብ ባደረጋቸው 51 ጨዋታዎች 21 ግቦችን ያስቆጠረበት ዓመት የተጫዋቹ የምን ጊዜም ምርጡ ወቅት ነበርም ተብሏል።
ከጋና ብሔራዊ ቡድን ጋር ዘጠኝ ዋንጫዎችን ያሸነፈው ራፋኤል በመጨረሻም የሚወደውን እግር ኳስ እየተጫወተ እያለ ህይወቱ አልፏል።