በተያዘው ዓመት አንድ ቢትኮይን በ100 ሺህ ዶላር ሊመነዘር እንደሚችል ተገጿል
የአንድ ቢትኮይን ዋጋ ምንዛሬ ከ50 ሺህ ዶላር በላይ መመንዘር ጀመረ፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ባለፉት ዓመታት ዋጋው አሽቆልቁሎ የነበረው የዓለም ምናባዊ ወይም ክሊፕቶከረንሲ መገበያያ ገንዘብ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።
በዚህ ምክንያት አሁን ላይ አንድ ቢትኮይን ከ50 ሺህ ዶላር በላይ በመመንዘር ላይ ሲሆን ይህም ከሁለት ዓመታት በኋላ የታየው ከፍተኛ ጭማሪ መሆን ችሏል።
የቢትኮይን ዋጋ በተከታታይ ጭማሪ ያሳየው አሜሪካ በምናባዊ መገበያያ ገንዘብ አክስዮን መሸጥ እና መግዛት እንደሚቻል ከፈቀደች በኋላ ሲሆን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የ15 ሺህ ዶላር ጭማሪ አሳይቷል።
የቢትኮይን ዋጋ ጭማሪ ካሳለፍነው ወር ጋር ሲነጻጸር የ16 በመቶ ጭማሪ አድርጓል የተባለ ሲሆን ካለፈው ዓመት ጥር ወር ጋር ሲነጻጸር ደግሞ በ150 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ከሁለት ዓመት በፊት የምናባዊ ወይም ክሪፕዮከረንሲ ግብይቶች ተፈላጊነታቸው መጨመሩን ተከትሎ አንድ ቢትኮይን እስከ 60 ሺህ ዶላር በመመንዘር ላይ ነበር።
የምናባዊ ገንዘብ ተቀባይነት በተለያዩ የዓለማችን ሀገራት እየጨመረ ቢመጣም እንደ ቻይና ያሉ ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት ግን እገዳ እንደጣሉ ናቸው።
ኤልሳልቫዶር ቢትኮይን እንደ አንድ የሀገሪቱ መገበያያ ገንዘብ አድርጋ የተቀበለች ሲሆን ሌሎችም ሀገራት ይህን በመከተል ላይ ይገኛሉ፡፡
በያዝነው አዲሱ የፈረንጆች 2024 ዓመት ውስጥ የቢትኮይን ዋጋ የሚጨምርበት ይሆናል የተባለ ሲሆን እስከ አንድ ቢትኮይን 100 ሺህ ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ባለሙያዎች ተንብየዋል፡፡
ኢትዮጵያ የትኛውንም የምናባዊ መገበያያ ገንዘብ የከለከለች ሲሆን ይህን አሰራር በህግ መምራት የሚያስችል ህግ በማዘጋጀት ላይ መሆኗን አስታውቃለች።