ከኮሮና ክትባት ጋር በተያያዘ እክል ለሚገጥማቸው የ92 ሀገራት ዜጎች ካሳ ይከፈላል ተባለ
ኢትዮጵያ በኮቫክስ ስርዓት ከታቀፉ ሀገራት መካከል መሆኗ ይታወሳል
ካሳው ኮቫክስ በተሰኘው የክትባቶች ግዢ ስርዓት ለታቀፉ 92 ሀገራት ዜጎች ብቻ የሚከፈል ነው ተብሏል
ከኮሮና ክትባቶች ጋር በተያያዘ እክል ለሚገጥማቸው የክትባቶቹ ተጠቃሚዎች ካሳ ለመክፈል የሚያስችል አዲስ የካሳ መርሃ ግብር ሊዘረጋ ነው፡፡
መርሃ ግብሩ በዓለም የጤና ድርጅት እና ቸብ (Chubb Limited) በተባለ ኩባንያ ትብብር የሚዘረጋ ሲሆን በዓለም አቀፉ የክትባቶች ትብብር (ጋቪ) ስር በተቋቋመው የኮሮና ቫይረስ ዓለምአቀፍ ተደራሽነት (ኮቫክስ) የታቀፉ 92 ሀገራት ዜጎችን ብቻ የሚመለከት ነው ተብሏል፡፡
እ.ኤ.አ እስከ ሰኔ 30/2022 ድረስ በኮቫክስ በኩል ከሚሰራጩ ክትባቶች ጋር በተያያዘ ከባድ እክል ሊገጥማቸው የሚችል የትኛውም የተጠቀሱት ሃገራት ዜጎችን እንደሚመለከትም ነው የተገለጸው፡፡
92ቱ ሀገራት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ምጣኔ ሃብት አላቸው በሚል ተለይተው የጋቪ ቦርድ እውቅና የሰጣቸው መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያም ዝቅተኛ እና መካከለኛ ምጣኔ ሃብት አላቸው በሚል በኮቫክስ ስርዓት ከታቀፉ ሃገራት መካከል መሆኗ አይዘነጋም፡፡
በኮቫክስ አማካኝነት የሚሰራጩ ሁሉም ክትባቶች የደህንነት እና የውጤታማነት ማረጋገጫ የተሰጣቸው መሆናቸውንም ነው የዓለም ጤና ድርጅት በድረ ገጹ ያስታወቀው፡፡ ይሁንና ፈቃድ ያገኙ የትኞቹም መድኃኒቶች እና ክትባቶች እንደሚኖራቸው የጎንዮሽ ጉዳት ሁሉ ፣ የኮቫክስ ክትባቶችም አልፎ አልፎ ከባድ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ ተብሏል፡፡
ከሚወስዱት ክትባት ጋር በተያያዘ እክል (የጎንዮሽ ጉዳት) ለሚገጥማቸው የሚከፈለው የካሳ አገልግሎት መርሃ-ግብር በኮቫክስ ድረ ገጽ (www.covaxclaims.com) በአውሮፓውያኑ መጋቢት 31/2021 እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡ መርሃ-ግብሩ ሲጀምር በክትባቱ ጉዳት ደርሶብናል የሚሉ ሰዎች ፣ ክትባቱን የወሰዱት ከመጋቢት 31 በፊት ቢሆን እንኳን ፣ ለካሳ ክፍያ ማመልከት ይችላሉ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ከ’ቸብ’ (Chubb) ጋር በመተባበር ለመርሃ-ግብሩ የመድህን አገልግሎት ለመስጠት በመስራት ላይ መሆኑን የገለጸ ሲሆን ‘ቸብ’ በመሪነት መድህኑን ይሸፍናል ተብሏል፡፡