የተመድ ዋና ጸኃፊ እስካሁን 130 ሀገራት ምንም ክትባት እንዳልደረሳቸውና 75 በመቶ የሚሆነው ክትባት በ10ሩ ሀገራት መሰራጨቱን ገልጸዋል
የኮሮና ቫይረስ ክትባት በዓለም አቀፍ ደረጃ መሰራጨት ሲገባው በ10 ሀገራት ቁጥጥር ስር ብቻ መዋሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አስታወቁ፡፡
ዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ 130 ሀገራት አንድም የኮሮና ክትባት እንዳልደረሳቸው ገልጸው 75 በመቶ የሚሆነው ክትባት ግን በ10 ሀገራት ብቻ እየተሰራጨ መሆኑን ገልጸዋል፡፡አሁን ላይ ያለው ስርጭት እጅግ ፍትሃዊ አለመሆኑን ያኑሰት ዋና ጸሐፊው ሊስተካከል እንደሚገባል ብለዋል፡፡
ይህንን የበዛ አድሎ ለመከላከልና ስርጭቱን ፍትሐዊ ለማድረግ ዋና ጸሐፊው የቡድን 20 አባል ሀገራት የድንገተኛ ግብረ ኃይልን እንዲቋቋም ውሳኔ አቅርበዋል፡፡ የድንገተኛ ግብረ ኃይሉ የክትባቱ ስርጭት ለአፍሪካና ለደቡብ አሜሪካ ሀገራት ጭምር እንዲዳረስ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከተመድ የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አባላት ጋር ባደረጉት የበይነ መረብ ስብሰባ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የክትባቱ ፍትሀዊነት ትልቁ የሞራል ፈተና እንደሆነ አንስተዋል፡፡ በዓለም ላይ እስካሁን 188 ሚሊዮን ብልቃጥ የኮሮና ክትባት መሰራጨቱ የተገለጸ ሲሆን በአስር ሚሊዮኖች ብልቃጥ የሚቆጠረው መድሀኒት ግን ወደ አሜሪካ፣ ቻይና፣ብሪታኒያና እስራኤል ነው የተሰራጨው፡፡
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ 10 ሀገራት ከ 75 በመቶ በላይ የኮሮና ክትባትን እየተቆጣጠሩ ነው ቢሉም የሀገራቱን ስም ግን አልዘረዘሩም፡፡ ይሁንና 72.4 ሚሊዮን ብልቃጥ ክትባትን በሀገሯ ያሰራጨችው አሜሪካ ከነዚህ 10 ሀገራት አንዷ እንደምትሆን እየተገመተ መሆኑን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ዋና ጸሐፊው እንዲቋቋም የወሰኑት ግብረ ሃይል ቀደም ሲል የዓለም ጤና ድርጅት እና የክትባቶች ጥምረት ክትባት ለመግዛትና ለማሰራጨት ካለባቸውን ኃላፊነት ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ የክትባቶች ጥምረት 2 ቢሊዮን ብልቃጥ ክትባቶችን ለማቅረብ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡