ኢትዮጵያ በመጀመሪያ የኮቪድ-19 ክትባትን 20በመቶ ለሚሆነው ህዝቧ ለመስጠት ማቀዷን ገለጸች
በኢትዮጵያ እስካሁን 1937 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ህይወታቸውን አጥተዋል
ሚኒስትር ዴዔታዋ ክትባቱ ለ270ሺ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎች ተጋላጭ ማህበረሰቦች ቅድሚያ ይሰጣል ብለዋል
የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ለጤና ባለሙያዎችና ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ቅድሚያ በመስጠት 20 በመቶ ለሚሆነው የሀገሪቱን ህዝብ በመጀመሪያ ዙር የኮቪድ-19 ክትባትን ለመስጠት ታቅዷል፡፡
ሚኒስትር ዴዔታ ሳህርላ አብዱላሂ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አሁን ቅድሚያ የሚሰጣቸው ቦታዎች መለየታቸውን እና የላቦራቶሪ ሂደቶችን በመለየት ዝግጅቶች እየተካሄዱ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስትር ዴዔታዋ እንዳሉት የኮሮና ክትባት ወደ ሀገር ከመጣና ውጤታማነቱ ከተረጋገጠ በኋላ 270 ሺ የሚሆኑ የጤና ባሙያዎችና ሌሎች ተጋላጭ ማህበረሰቦች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡
ክትባቱን ለመስጠት የሚስችሉ ስራዎች ከሶስት ወራት በፊት መጀመራቸውን ተናግረዋል ሚኒስትር ዴዔታዋ፡፡
የቅርብ ጊዜ የኮሮና ፅኑ ህሙማን መጨመርና የጤና መጠበቂያዎች እጥረት የጤና ባለሙያዎችንና አጠቃላይ የጤና ዘርፉን ባለሙያዎች ተጋላጭ አድርጓቸዋል፡፡
የኮሮና ክትባት ድጋፍን ኮቫክስን ከመሳሰሉትና ከሌሎች ሀገራት ድጋፍ እንደሚያገኝ የተናገሩት ሳህራላህ ኢትዮጵያ የኮቫክስ ቦርድ አባል ናት ይህም የኮቪድ-19 መከላከያ መሳሪያዎችን ለማግኘት አንዱ ምሰሶ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ እስካሁን ከ124 ሺ 652 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 112 ሺ 251 ሰዎች ከበሽታው ሲያገግሙ 1 ሺ 937 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል፡፡
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 10 ሺ 462 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው የጤና ሚኒስቴር በትናንትናው እለት ያወጣው መግለጫ ያሳያል፡፡