ባለሙያው ክትባቱን ከወሰደ ከአንድ ሳምንት በኋላ በተደረገለት ምርመራ ቫይረሱ እንደተገኘበት አስታውቋል
በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት የኮሮና ቫይረስ ክትባትን (የፋይዘር ክትባት) የወሰደ የህክምና ባለሙያ በቫይረሱ መያዙን አስታወቀ፡፡
የ45 ዓመቱ ነርስ የፋይዘር ክትባትን ከወሰደ ከአንድ ሳምንት በኋላ ባደረገው የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ቫይረሱ እንደተገኘበት መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በሁለት ሆስፒታሎች እያገለገለ ያለው ማቲው በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ እንዳሰፈረው በፈረንጆቹ ታህሳስ 18 ቀን 2020 የፋይዘር ክትባትን መውሰዱን ገልጿል፡፡ክትባቱን ከወሰደ በኋላ ለአንድ ቀን ያህል ክንዱ ላይ የህመም ስሜት ተሰምቶት እንደነበረና ከዛ ውጭ ግን ምንም የተለየ ስሜት እንዳልተሰማው ገልጾ ነበር፡፡ ክትባቱን ከወሰደ ከስድስት ቀን በኋላ ግን የህመም ስሜት እንደተሰማው የገለጸው ማቲው ባደረገው የኮሮና ምርመራ ቫይረሱ እንዳለበት ተናግሯል፡፡
ክትባት ወስዶ የኮሮና ቫይረስ የተገኘበትን ነርስ በተመለከተ አስተያየት የሰጡት የተላላፊ በሽታዎች ተመራማሪዋ ክርስቲያን ራመርስ ይህ የማይጠበቅ ክስተት አይደለም ብለዋል፡፡ ጉዳዩ ሊያጋጥም የሚችልና ተጠባቂ እንደሆነ የገለጹት ተመራማሪዋ አንድ ሰው ክትባቱን ከወሰድ በኋላ ቫይረሱን ለመከላከል ከ10 እስከ 14 ቀን ሊወስድበት እንደሚችል ተመራማሪዋ ገልጸዋል፡፡
የመጀመሪው ዙር ክትባት 50 በመቶ የመከላከል አቅም እንዳለውና የመከላከል አቅምን 95 በመቶ ለማድረስ ሁለተኛ ዙር ክባት እንደሚስፈልግም ነው ሮይተርስ የዘገበው፡፡ ባለሙያዋ ሁለተኛውን ዙር ክትባት መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡