“አርቲፋክት” የኢንስታግራም መስራቾቹ የፈጠሩት አዲሱ የማህበራዊ ትስስር ገጽ
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሚጠቀመው “አርቲፋክት” ዜናዎችን እንደሰው ፍላጎት የሚያቀርብ ነው
“አርቲፋክት” እንደ ፌስቡክ፣ ትዊተር እና ቲክቶክ ያሉ ማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚጠቀሟቸው ሰው ሰራሽ አስተውሎቶች አይነት ነው ተብሏል
የኢንስታግራም መስራቾቹ በአዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራ መመለሳቸውን አስታወቁ።
ኪቪን ሲስቶርም እና ማይክ ክሪገር ከማህበራዊ ትስስር ገጹ ከለቀቁ ከአራት አመት በኋላ ነው “አርቲፋክት” የተሰኘ አዲስ መተገበሪያን ያስተዋወቁት።
“አርቲፋክት” የተመረጡ ዜናዎችን የሚያቀርብና ደንበኞቹ ቀደም ብሎ የነበራቸውን የፍለጋ ታሪክ በመቃኘት ይስማማቸዋል ብሎ የሚገምተውን የሚጠቁም ሰው ሰራሽ አስተውሎትን የሚጠቀም መተግበሪያ ነው።
የመተግበሪያው መተዋወቅ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሰው ሰራሽ አስተውሎት ድርሻ ከፍ እያለ መሄዱን ያሳያል ተብሏል።
እንደ ፌስቡክ እና ትዊተር ያሉ የማህበራዊ ትስስር ገጾች የተጠቃሚዎችን የፍለጋ ታሪክ እየቃኙ ዜናዎችን፣ ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን ወደገጻችን እንዲመጣ የሚያደርጉ ሰው ሰራሽ አስተውሎቶችን ይጠቀማሉ።
ቲክቶክም እንዲሁ ደጋግመን ካየነው ቪዲዮ በመነሳት “ለእርስዎ ይሆናል” የሚል አማራጭን ያስቀምጣል፤ በተደጋጋሚ ካየናቸው ምስሎች ጋር የሚመሳሰሉ ቪዲዮዎችንም በዚሁ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ይለቃል።
አዲሱ “አርቲፋክት” መተግበሪያም ቲክቶክ ደጋግመን ያየናቸውን ምስሎች እየተከታተለ የተቀራረበውን እንደሚያስመለክተን ሁሉ ዜናዎችን የሚጠቁም ነው ተብሏል።
በዚህም በርካታ ዜና የሚያቀርቡ ኩባንያዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
“አርቲፋክት” ከዚህ ቀደም ዛይት እና ፐልስ ያቀርቡት የነበረውን አገልግሎት አሻሽሎ ማቅረቡን የቀድሞው የኢንስታግራም መስራቾቹ ተናግረዋል።
ለአብነትም የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ድረገጽን የጎበኘ አንድ አንባቢ በከፈተው ዜና ስር “አርቲፋክት” ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን የጋዜጣውን እና የሌሎች ድረገጾችን ዜናዎች ይዞ ብቅ ይላል።
በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የምንከተላቸው ሰዎች በዜናው ዙሪያ የሰጡትን አስተያየትም ያሳየናል።
መተግበሪያው ሰዎች የሚፈልጓቸውን ዜናዎች በፍጥነት እና በብዙ አማራጭ ይዞ በመቅረብም ትልቅ ትስስር እንደሚፈጥር ኪቪን ሲስቶርም እና ማይክ ክሪገር ተናግረዋል።
የማህበራዊ ትስስር ገጾች የደንበኞቻቸውን የልብ ትርታ ለመረዳትና ተደራሽነታቸውን ለማስፋት እያገዙ የሚገኙት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎች አሉታዊ ተጽዕኗቸውም በጥናት ተደርሶበታል።
ወል ስትሪት ጆርናል ባለፈው አመት በቲክቶክ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም ላይ ባደረገው ጥናት፥ ህጻናት ለረጅም ስአታት ቲክቶክን መጠቀማቸው የምግብ ፍላጎታቸውን ክፉኛ እንደጎዳው አመላክቷል።
ለዚህም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂው ደጋግመው ያዩትን እየመዘገበ የሚፈልጉትን የማቅረቡ ነገር አንዱ ምክንያት ተደርጎ ተወስዷል።
በፌስቡክ እና ትዊተርም አሉታዊ ነገሮች በፍጥነት እንዲሰራጩ የነዚህ ቴክኖሎጂዎች አበርክቶ ቀላል አለመሆኑን ባለሙያዎች ያነሳሉ።
የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ግን በዚህ አይስማሙም፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት በመረጃ አቅራቢውና ፈላጊው መካከል ትስስርን ለመፍጠር ድርሻ እንዳላቸው ይሞግታሉ።
የሰው ልጅን ፍላጎት መረዳት ለሚቀርበው አገልግሎት ስኬታማነት መሰረት ይጥላል እንጂ ችግር የሚፈጥር አይደለም የሚል መከራከሪያም አላቸው።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት በማህበራዊ ትስስር ተጠቃሚዎች ላይ የፈጠሩት ተጽዕኖ በቀጣይ በሌሎች ጥናቶች የሚታይ ቢሆንም፥ ቴክኖሎጂውን ለማዘመን የሚደረጉ ጥረቶች ግን ቀጥለዋል።