ማህበራዊ ሚዲያ- አዲሱ የወሲብ ንግድ ሜዳ
በይነ መረብ እና ማህበራዊ ሚዲያዎች ሰዎች ከዚህ በፊት ወሲብ ፍለጋ ወደ ምሽት ቤቶች ያደርጉት የነበረውን ጊዜ ማሳጠራቸው ይነገራል
ይህ መሆኑ የወሲብ ንግድን ከማቅለልም በላይ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ስርጭትን በእጅጉ አሳድጓል ነው የሚባለው
በኢትዮጵያ ከ622 ሺህ በላይ ሰዎች የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው የሚገኝ ሲሆን በአማካኝ 12 ሺህ ሰዎች ደግሞ እንደ አዲስ በየ ዓመቱ በቫይረሱ ይያዛሉ፡፡
የቫይረሱን ስርጭት የከፋ የሚያደርገው በየ ዓመቱ በቫይረሱ ከሚያዙ ሰዎች ውስጥ 67 በመቶዎቹ እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች እንደሆኑ የፌደራል የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት ሪፖርት ያስረዳል፡፡
የዚህ ገዳይ ቫይረስ ስርጭትን እና የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ከዚህ በፊት በተሰሩ ስራዎች ከነበረበት የወረርሽኝ ደረጃ አሁን ላይ የስርጭት ምጣኔውን ወደ 0 ነጥብ 86 ማድረስ ቢቻልም አሁን ግን የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ እንደሆነ ይነሳል፡፡
የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር በዋነኝነት የቫይረሱ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተለያዩ መንገዶች በመድረስ የግንዛቤ እና የህክምና አገልግሎት መስጠት ተችሎ ነበር፡፡
ሁሉም ዜጋ ካልተጠነቀቀ ለቫይረሱ ተጋላጭ ቢሆንም በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ሰዎች፣ ታራሚዎች፣ የረጅም መንገድ አሽከርካሪዎች፣ ባላቸው የሞተባቸው እናቶች ወይም የፈቱ ሴቶች፣ ተንቀሳቃሽ ሰራተኞች እና አንዱ የትዳር አጋራቸው በቫይረሱ የተያዘባቸው ሰዎች ይበልጥ ተጋላጮች ናቸው፡፡
ከላይ በተገለጹት ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ በተሰሩ ስራዎች የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ ቢቻልም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የበይነ መረብና የማህበረሰብ ትስስር ገጾች የሰዎችን ትውውቅ ቀላል በማድረግ ብዙ መልካም ስራዎችን ማከናወን ቢያስችሉም የራሳቸው ጉዳት ደግሞ አላቸው፡፡
በይነ መረብ እና ማህበራዊ ሚዲያዎች ሰዎች ከዚህ በፊት ወሲብ ፍለጋ ወደ ምሽት ቤቶች ያደርጉት የነበረውን ጊዜ በማሳጠሩ የወሲብ ንግድን ቀላል እንዳደረገው የማህበረሰብ ጤና አማካሪው ዶክተር አምሃ ሀይሌ ነግረውናል፡፡
ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያዎች እያደረጓቸው ያሉ እንቅስቃሴዎች እንደ አገር ተቀርጾ የነበረውን የሴተኛ አዳሪነት ትርጉም እንዲከለስ አስገድዷልም ብለዋል ዶክተር አምሃ፡፡
ከዚህ በፊት በነበረው ኤች አይ ቪ ኤድስ ይበልጥ ተጋላጭ ተብለው የተለዩት ሴተኛ አዳሪዎች፣ ታራሚዎች፣ የረጅም መንገድ አሽከርካሪዎች፣ ባላቸው የሞተባቸው እናቶች ወይም የፈቱ ሴቶች፣ ተንቀሳቃሽ ሰራተኞች እና አንዱ የትዳር አጋራቸው በቫይረሱ የተያዘባቸው ሰዎች እንደነበሩ የገለጹት ዶክተር አምሃ በይነ መረብ እና ማህበራዊ ሚዲያዎች የአዲሱ ትውልድ የወሲብ መገበያያ ቦታዎች ሆነዋል ብለዋል፡፡
ኦን ላየን ፕላትፎርም ላይ ያሉ በወሲብ ንግድ የሚሳተፉ ሰዎችን መለየት ያስፈልጋል የሚሉት አማካሪው ከዚህ በፊት የነበረው የሴተኛ አዳሪነት ትርጉም በወሲብ ንግድ የሚተዳደር ቢሆንም አሁን ግን አገልግሎቱን ኦን ላይን መሸጥ ተጀምሯል፡፡
ይሁንና አሁን ነገሮች እየተቀየሩ በመሆኑ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያሉ ሴተኛ አዳሪዎችን መድረስ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ የግድ እነሱን የሚመጥን ይዘት፣ በጀት ተመድቦለት መሰራት እንደሚጠበቅ ዶ/ር አምሃ ገልጸዋል፡፡
“የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ በተለይም ሴተኛ አዳሪዎችን ለመድረስ በተለየ መንገድ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ በፊት የግድ ሴተኛ አዳሪዎችን ለማግኘት ወደ ምሽት ቤቶች መሄድ የግድ ይላቸው ነበር አሁን ግን ሁሉም ነገር ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ አሉላቸው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ የቫይረሱን ስርጭት ያሳድገዋል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያዎች በራሳቸው ችግር ባይሆኑም ሁሉንም የሚመጥን ይዘት መተግበር ያስፈልጋል“ብለዋል፡፡
ከባዱ ነገር እነዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ወሲብ ነጋዴዎች ራሳቸውን እንደ ወሲብ ነጋዴዎች ስለማይቆጠሩ የጥንቃቄ እርምጃዎችን አለመውሰዳቸው እና ከተለያዩ ሰዎች ጋር ወሲብ እንደቀላል መፈጸማቸው ነውም ብለዋል ዶክተር አምሃ፡፡
የመንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየተካሄዱ ያሉ የወሲብ ንግዶች ግንዛቤው አላቸው ብዬ አላምንም የሚሉት ዶ/ር አምሃ ወጣቶች ላይ ያተኮሩ መልዕክቶችን ማዘጋጀት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በባህሪያቸው “ስልቹ” ስለሆኑ መልዕክቶቹ ፈጠራን መሰረት ያደረጉ ሳቢ እና አጠር ብለው የተዘጋጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡
አማካሪው ከዚህ በተጨማሪም ብዙ አገራት እንደሚያደርጉት የወሲብ ንግዶችን የሚያበረታቱ የትስስር ገጾችም በቀላሉ ለሁሉም ህብረተሰብ እንዳይደርሱ መንግስት ቁጥጥር ማድረግ አለበት ያሉም ሲሆን ህብረተሰቡ በቀላሉ በነዚህ መልዕክቶች እንዳይታለል እና ጎጂ መልዕክቶችን በራሱ መንገድ እንዲከላከል የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎችንም ማከናወን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
በፌደራል የኤች አይቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት የዘርፈ ብዙ ምላሽ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ክፍሌ ምትኩ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በየዓመቱ በቫይረሱ ከሚያዙት 622 ሺህ በላይ ዜጎች መካከል የወጣቶች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቫይረሱ በብዛት ወጣቶችን ሊያጠቃ የቻለበት ምክንያት ስለ ቫይረሱ የሚያገኙት መረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እና ትኩረት እየተነፈገው በመምጣቱ ነው እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፡፡
“ ማህበራዊ ሚዲያዎች ብዙ ጠቃሚ እና ጎጂ መረጃዎች ይለቀቃሉ በዚያው ልክ ግን ወጣቶችን የሚመጥን መረጃ እየተሰራ አይደለም” የሚሉት አቶ ክፍሌ ተቋማቸው መረጃዎችን በተለመደው መንገድ እያቀረበ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡
አሁን ላይ ወጣቶችን ኤች አይ ቪን ጨምሮ ለተለያዩ በሽታዎች የሚያጋልጡ መረጃዎች በማህበራዊ የትስስር ገጾች ለወጣቶች በገፍ እየተለቀቁ እንደሆነ ብንረዳም ያንን የሚመጥን ስራ እየተሰራ አይደለም፣ ይህ ስራ የሁሉም ተቋም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ ወሲብን የሚያበረታቱ የበይነ መረብ ትስስር ገጾች በብዛት ወደ ህብረተሰቡ እንዳይደርሱ የሚያደርግ አሰራር አላችሁ? ሲል የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳድርን ጠይቋል፡፡
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ይግዛው (ዶ/ር) በበኩላቸው ወሲብን የሚያበረታቱ ድረገጾች እና የማህበራዊ ትስስር ገጾች እንዲዘጉ በየጊዜው ጥያቄዎች እንደሚቀርቡ ተናግረዋል፡፡
“ሁሉም የበይነ መረብ ገጾች አገልግሎቱን እያቀረቡ ነው በእኛም አገር ይህ እየሆነ ነው፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን በማገድ ብቻ ልናስቆመው አንችልም፡፡ መፍትሄው ሰዎች የሚጠቅማቸውን እና የሚጎዳቸውን የትስስር ገጾች መለየት አለባቸው፡፡” ብለዋል፡፡
ተጠቃሚው አገልግሎቱን ተገዶ የሚያገኘው ባለመሆኑ የሚያየውን ሊመርጥ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡
ቴክኖሎጂው ወደ ታዳጊ አገራት የገባው በቅርብ ጊዜያት ሊያውም ደግሞ ብዙም ሳይዘጋጁበት ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ ልክ ቀስ በቀስ ጥቅምና ጉዳቱን ለይተው አጠቃቀሙን እንዳዳበሩት እንደ ምዕራባውያን ሁሉ የዲጅታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እውቀት (ዲጅታል ሊትሬሲ) ጉዳይ በኢትዮጵያም ማደግ አለበት፡፡
የወሲብ ንግድን የሚያበረታቱ የማህበራዊ ትስስር ገጾች እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ታዳጊ አገራት ይልቅ በበለጸጉ አገራት ይበዛሉ፡፡ ይሁን እንጂ የእኛ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ትክክል ባለመሆኑ ለኤች አይቪ ኤድስ እና ለመሰል በሽታዎች በቀላሉ መስፋፋት ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸው ይነገራል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ሆኖ እነዚህ የቴክኖሎጂ የትስስር ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ ባህል እና ወግ ጋር የማይሄዱ ይዘቶችን እንዳይለቁ እና እንዳያሰራጩ ከኩባንያዎቹ ጋር ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን አክለዋል፡፡