የዓለም ሃገራት ሚኒስትሮች የሚሳተፉበት ግዙፍ ጉባዔ በቅርቡ በስቶኮልም ይካሄዳል
በመላው ዓለም በዓመት 1 ነጥብ 3 ሚሊዬን ሰዎች በትራፊክ አደጋ ይሞታሉ
የዓለም የጤና ድርጅት በመላው ዓለም በየዓመቱ 1 ነጥብ 3 ሚሊዬን ሰዎች በትራፊክ አደጋ ይሞታሉ ብሏል፡፡
እ.ኤ.አ በ2030 ሞቱን በግማሽ ለመቀነስ ከ1 መቶ የሚልቁ ሃገራት ሚኒስትሮች ከ2 ሳምንት በኋላ በስዊድን ስቶኮልም ተገናኝተው እንደሚመክሩም አስታውቋል፡፡
አደጋው እጅግ አሳዛኝ ችግሮችን እየፈጠረ እንደሆነ የተናገሩት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ሊሆን የማይገባ ዋጋ እየተከፈለ ይገኛል ብለዋል፡፡
በቅርቡ የወጡ ዓለም አቀፍ የመንገድ ደህንነት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ከ5 እስከ 29 በሚደርስ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህጻናትን እና ወጣቶችን ህይወት ከሚቀጥፉ መንስዔዎች መካከል የትራፊክ አደጋ ቀዳሚው ነው፡፡
አደጋው በዋናነት እግረኞችን፣ብስክሌተኞችን እና ሞተረኞችን ሰለባ ያደርጋል፡፡ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሃገራት ዜጎች ናቸው በአደጋው እጅግ ተጎጂው፡፡ ከፍተኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት በ3 እጥፍ የሚበልጥ አስከፊ አደጋንም ያስተናግዳሉ፡፡
በዓመት እስከ 50 ሚሊዬን የሚደርሱ ሰዎችም ቀላል የሚባሉ የትራፊክ አደጋዎችን እንደሚያስተናግዱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ሊያመጣ የሚችለው ምጣኔ ሃብታዊ ድቀት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
ብዙዎቹን አደጋዎች ልንከላከላቸው የሚችሉ ናቸው የሚሉት ዶ/ር ቴድሮስ ሚኒስትሮቹን የሚያሰባስበው ኮንፍረንስ አደጋውን ለመቀነስ የሚያስችሉ አዳዲስ አጀንዳዎችን ለማስቀመጥ የሚያስችል መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
በኮንፈረንሱ የትራንስፖርት፣የጤና ሚኒስትሮችን እና የመንግስታቱ ድርጅት ተወካዮችን እንዲሁም ምሁራንን ጨምሮ ከ1 ሺ 5 መቶ በላይ ልዑካን ይሳተፋሉ፡፡
ከሚኒስትሮቹ ኮንፈረንስ በፊት ዕቅዱን ከዳር ለማድረስ እንደሚያስችል የታመነበት “ስቶኮልም ዲክላሬሽን” እንደሚዘጋጅና በኮንፈረንሱ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል፡፡