ግሎባል ቴሌቭዥን ኔትወርክ ኦፍ አፍሪካ ዋና መቀመጫውን አዲስ አበባ አድርጎ በ15 ሀገራት ዘጋቢዎችን ይዞ ስራ እንደሚጀምር ተገለፀ
ሚዲያው የአፍሪካን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ በእንግሊዘኛ ቋንቋ በቅርቡ ወደ ተመልካች እደርሳለሁ ብሏል
ባለ 63 ወለል ህንጻ ለመገንባት 5 ሺህ ካሬ ቦታ በአዲስ አበባ መረከቡንም ሚዲያው ገልጿል
ግሎባል ቴሌቭዥን ኔትወርክ ኦፍ አፍሪካ ዋና መቀመጫውን አዲስ አበባ አድርጎ በ15 ኀገራት ዘጋቢዎችን ይዞ ስራ እንደሚጀምር ተገለፀ።
በጋዜጠኛ ግሩም ጫላ በምስረታ ላይ ያለው ግሎባል ቴሌቭዥን ኔትወርክ ኦፍ አፍሪካ በእስካሁኑ እና ስለቀጣይ የተቋሙ እቅድ ዙሪያ ለብዙሃን መገናኛዎች መግለጫ ሰጥቷል።
በመገልጫው ላይ እንደተጠቀሰው፤ ይህ ሚዲያ ዋና ዓላመው ስለ አፍሪካ ተዓማኒ መረጃዎችን ለዓለም ማህበረሰብ በማድረስ የአፍሪካ ድመጽ መሆን ነው።
በምስረታ ላይ ያለው ይህ ሚዲያ ዋና መቀመጫውን በአዲስ አበባ በማድረግም በእንግሊዘኛ ቋንቋ የአፍሪካን መልካም ስም ማጎልበት የሚያስችሉ ይዘቶችን ለዓለም እንደሚያደርስ የሚዲያው ስራ አስፈጻሚ ጋዜጠኛ ግሩም ጫላ ተናግሯል።
ይህ ሚዲያ መቼ ለተመልካቾች መተላለፍ ይጀምራል? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም “ስርጭታችን በዚህ ጊዜ ይደርሳል አንልም ግን ለዚያ የሚያበቃንን ስራዎች በፍጥነት በማከናወን ላይ ነን። ፕሮጀክት ቢሮ ከፍተን ስቱዲዮ እንገነባለን ከዚያ አዲስ አበባን ጨምሮ በአፍሪካ ከ10 እስከ 15 ወኪል ዘጋቢዎችን እንዲሁም ከአፍሪካ ውጪ ኒዮርክ፣ ቤጂንግ እና ለንደን ሆነው የሚዘግቡ ጋዜጠኞችን ይዘን ስራ እንጀምራለን“ ሲሉ ምለሽ ሰጥተዋል።
ግሎባል ቴሌቭዥን ኔትወርክ ኦፍ አፍሪካን ለማቋቋም ከሶስት እስከ 5 ቢሊየን ብር ያስፈልጋል ያሉት ስራ አስፈጻሚው ገንዘቡን ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ የንግድ ሰዎች እና ተቋማት በአክስዮን ሽያጭ ለማሰባሰብ መታቀዱንም አክለዋል።
እስካሁን ባለው የቅድመ ዝግጅት ስራም የሚዲያውን ዋና ቢሮ ባለ 63 ወለል ህንጻ መገንባት የሚያስችል 5 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር መረከባቸውንም ጋዜጠኛ ግሩም በመግለጫው ላይ ተናግሯል።
የኢንቨስትመንት ፈቃድ፣ የንግድ ምዝገባ፣ የቦርድ አባላት ምርጫ እና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀዋል የተባለ ሲሆን፤ የስርጭት ፈቃድ ማግኘት፣ የስራ ቅጥር እና የስራ ስልጠናዎች በቀጣይ እንደሚጀመሩም ተገልጿል።