ግዙፍ የሚዲያ ተቋማት ድረ ገጾች ባልታወቀ ምክንያት ከአግልግሎት ውጪ ሆነው ቆይተዋል
የሲ.ኤን.ኤን፣ ብሉምበርግ ኒውስ፣ ፋይናንሻል ታይምስና ሌሞንዴ ጋዜጣ ድረ ገጾች ስራ አቁመው ነበር
የድረ ገጾች መቋረጥ ያጋጠመው ‘ፋስትልይ’ የክላውድ አገልግሎት አቅራቢ ኩባንያ ውስጥ በገጠመ እክል ነው ተብሏል
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ግዙፍ የሚዲያ ተቋማትን ጨምሮ የበርካታ ድርጅቶች ድረ ገጸች ከአገልግሎት ውጪ ሆነው እንደነበረ ተገለጸ።
ድረ ገጾች ዛሬ ጠዋት ላይ እስካሁን ምንነቱ ባልታወቀ ምክንያት ከስራ ውጪ ሆነው እንደነበረም ነው የሮይተርስ ዘገባ የሚያመለክተው።
ድረ ገጻቸው እና መተግበሪያቸው ከአገልግሎት ውጪ ሆነው ከነበሩ ድረ ገጾች ውስጥም ሲ.ኤን.ኤን፣ ብሎምበርግ ኒውስ፣ ፋይናንሻል ታይምስ፣ የፈረንሳዩ ሌሞንዴ ጋዜጣ፣ ይገኙበታል የተባለ ሲሆን፤ ቢቢሲ እና ኒውዮርክ ታይምስም በጊዜያዊነት ስራ አቁመው ነበረ ተብሏል።
የአማዞን፣ ፔይ ፓል፣ ሬዲት፣ ሰፖቲፊ የተባሉ ድርጅቶች ድረ ገጾችም ከአገልግሎት ውጪ ሆነው እንደነበረም ተነግሯል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት ዋና ድረ ገጽ (gov.uk) እና የአሜሪካው ዋይት ሀውስ ድረ ገጽም ጊዜያዊ የአገልግሎት መቋረጥ አጋጥሟቸው እንደነበረም ታውቋል።
ድረ ገጾቹ የተቋረጡት ዛሬ ጠዋት ላይ ሲሆን፤ ሰዎች ድረ ገጾቹን በሚከፍቱበት ጊዜም “Error 503 Service Unavailable” እና “connection failure” የሚሉ ጽሁፎች ይታዩ ነበረ ተብሏል።
የችግሩ ዋነኛ መንስኤ እስካሁን በግልጽ ባይታወቅም፤ ‘ፋስትልይ’ ከተባለ ለግዙፍ ታቋማት የክላውድ አገልግሎት አቅራቢ ኩባንያ ውስጥ በገጠመ እክል የድረ ገጾች መቋረጥ መፈጠሩ ተነግሯል።
መቀመጫውን አሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ ያደረገው ‘ፋስትልይ’ የክላውድ አገልግሎት አቅራቢ ኩባንያ ችግሩ ማጋጠሙን በማረጋገጥ፤ የማስተካከያ እርምጃ እንደወሰደ አስታውቋል።
ችግሩ በምን ምክንያት እንደተፈጠረ ለመለየት የምርመራ ስራ መቀጠሉንም ነው ኩባንያው የገለጸው።
ከአግልግሎት ውጪ ሆነው የነበሩ በርካታ ድረ ገጾች ከረፋዱ 5 ሰዓት ጀምሮ መስራት ጀምረዋል።