የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ለአራት የውጭ ሀገር ሚዲያዎችን አስጠነቀቀ
ማስጠንቀቂያው ለሲ.ኤን.ኤን፣ ቢቢሲ፣ ሮይተርስ እና አሶሺዬትድ ፕረስ ነው የተሰጠው
ከድርጊታቸው የማይታቀቡ ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰሩ የተሰጣቸው የሥራ ፈቃድ እንደሚሰረዝ አስታውቋል
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ለአራት የውጭ ሀገር መገናኛ ብዙኃን ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታወቀ።
ከሰሞኑ የተወሰኑ የውጭ ሀገራት መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያን በተመከተ የተለያዩ የተዛቡ እና ሀሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጩ እንደሆነ መንግስት ማስታወቁ ይታወሳል።
በተለይም ለሲ.ኤን.ኤን፣ ቢቢሲ፣ ሮይተርስ እና አሶሺዬትድ ፕረስ የተባሉ የውጭ ሀገራ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያን በተመለከተ በሚያቅርቡት ዘገባዎቻቸው መንግስትን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት እና ግለሰቦችም ጭምር ሲተቹ መቆየቱም አይዘነጋም።
ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ለአራት የውጭ ሀገር መገናኛ ብዙኃን ማስጠንቀቂያመስጠቱን በዛሬው እለት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ የተላከላቸው የውጭ ሀገራት መገናኛ ብዙሃንም ሲ.ኤን.ኤን(CNN)፣ ቢቢሲ(BBC) ፣ ሮይተርስ (Reuters) እና አሶሺዬትድ ፕረስ (Associated Press) መሆናቸውን ባለስልጣኑ ገልጿል።
የመገናኛ ብዙሃኑ የህወሓት አካላትን ለመደገፍ ኢትዮጵያን በተመለከቱ ሀሰተኛ ዜናዎችን በማዘጋጀት እና በማሰራጨት እንዲሁም ትንታኔዎችን ማዘጋጀታቸውን በላከላቸው ደብዳቤ ላይ አስታውቋል።
እንዲሁም መንግስት እያካሄደ ያለውን ህግ የማስከበር ዘመቻ የዘር ጭፍጨፋ ጦርነት አስመስሎ መዘገብ፣ መንግስት ሰብአዊ ድጋፎችን ለማድረስ የሚያደርጋቸውን ጥረቶች አሳንሰው የማቅረብ፣ መንግስት ረሃብንና አስገድዶ መድፈርን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመ እንደሆነ አስመስሎ ማቅረብ እና ሀገሪቱን የሚያስተዳድረው ተቋም ላይ ስም የሚያጠፉ ዘገባዎችን መስራታቸውን ገልጿል።
በተጨማሪም የሀገሪቱን መሪ በዓለም ቀአፍ ደረጃ እውቅና ለማሳጣት እና ዲፖሎማሲያዊ ጫናዎች እንዲበረቱ ለማድረግ ሀሰተኛ ዜናዎችን እያመረቱ እንደሆነም ባለስልጣኑ በላከላቸው ደብዳቤ ላይ አስታውቋል።
ባልስጣሉ በተለያዩ ጊዜያት ከተቋምቱ ጋር ንግግሮችን በሚያደርግም እስካሁን ተጨባጭ ማሻሻዎች እንዳልታዩም ገልጿል።
በቀጣይ ከዚህ ድርጊታቸው የማይታቀቡ ከሆነ ባለስልጣኑ በተሰጠው ስልጣን እና ሃላፊነት መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ የሰጣቸውን የሥራ ፈቃድ እንደሚሰርዝም አስጠንቅቋል።