በኳታሩ የአለም ዋንጫ ምርጥ ጎል ያስቆጠረው ማን ነው?
172 ጎሎች የተቆጠሩበት የአለም ዋንጫ በአንድ ጨዋታ በአማካይ 2 ነጥብ 7 ጎሎች ተስተናግደውበታል
ከእነዚህ ጎሎች ምርጧን ለመለየትም ፊፋ 10 እጩ ተፎካካሪዎችን ይፋ ያደረገ ሲሆን ተመልካቾች ድምጽ እንዲሰጡባቸው ተጠይቋል
64ቱ የኳታር የአለም ዋንጫ ጨዋታዎች 172 ጎሎችን አስተናግደዋል።
የተቆጥሩት ጎሎች በ1998 እና 2014 ከተመዘገበው የ171 ጎል በአንድ ብልጫ ያለው ነው።
በጨዋታ በአማካይ 2 ነጥብ 7 ጎሎች የተሰተናገዱበት የአለም ዋንጫ በጎል የታጀበ አስደናቂ ፉክክር የታየበት መሆኑን ተመልክተናል።
ከ172 ጎሎቹ ውስጥ የምርጦች ምርጧ የትኛዋ ናት የሚለውን መለየቱም ከባድ ሆኗል።
ፊፋ በትናንትናው እለት የኳታር የአለም ዋንጫ ምርጥ ጎል ውድድር ውስጥ የገቡ 10 ጎሎችን ይፋ አድርጓል።
1 ሳሌም አል ዳውሳሪ - አርጀንቲና
ሳኡዲ አረቢያ ከምድብ ሶስት አርጀንቲናን በመክፈቻ የምድብ ጨዋታ 2 ለ 1 በረታችበት ጨዋታ የአል ሁላሉ አጥቂ ሳሌም አል ዳውሳሪ ከግራ ጠርዝ ኢሚሊያኖ ማርቲኔዝ ላይ ያስቆጠራት ምርጥ ጎል በእጩነት ቀርባለች።
2 ሪቻልሰን - ሰርቢያ
ብራዚላዊው ሪቻርልሰን በምድብ የመጀመሪያ ፍልሚያ ላይ ሰርቢያ ላይ በ62ኛው ደቂቃ መሪ ያደረገችውን ጎል አስቆጥሯል። ከ11 ደቂቃ በኋላ ያስቆጠራት ሁለተኛ የመቀስ ምት ማራኪ ጎልም ከአስሩ ተፎካካሪዎች አንዷ ሆናለች።
3 ኮዲ ጋክፖ - ኢኳዶር
ለኔዘርላንድስ በሶስት የምድብ ጨዋታዎች ሶስት ጎሎችን ያስቆጠረው ኮዲ ጋክፖም ከምርጥ ጎል ተፎካካሪዎቹ ውስጥ ተካቷል። በግራ እግሩ ኳስ እንዳሻው የሚያሽሞነሙነው ጋክፖ ኢኳዶር ላይ ከርቀት ያስቆጠራት ጎልም በእጩነት ቀርባለች።
4 ኢንዞ ፈርናንዴዝ - ሜክሲኮ
የአለም ዋንጫው ምርጥ ወጣት ተጫዋች ኢንዞ ፈርናንዴዝ ለአርጀንቲና ሁለት የምድብ ጨዋታዎችን አላደረገም። ከተጠባባቂነት ተቀይሮ በገባበት የሜክሲኮ ፍልሚያ ግን አስደናቂ ጎል ማስቆጠር ችሏል። ለውሃ ሰማያዊዮቹ እና ነጭ ለባሾቹ የዋንጫ ጉዞም ትልቅ አበርክቶ ነበረው።
5 ቪሰንት አቡበከር - ሰርቢያ
ካሜሮን ከሰርቢያ ጋር ባደረገችው ጨዋታ ቪሰንት አቡበከር ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል። በ55ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው አቡበከር በ63ኛው ደቂቃ ጎል አስቆጥሮ 3 ለ 1 ስትመራ የነበረችውን ካሜሮን አቻ እንድትለያይ ትልቁን ስራ ሰርቷል። ያስቆጠራት ጎልም በመጀመሪያ ከጨዋታ ውጭ ናት ቢባልም በቪዲዮ በታገዘ ዳኝነት (ቫር) ጎል መሆኗ ተረጋግጧል።
6 ልዊስ ቻቬዝ - ሳኡዲ አረቢያ
ሜክሲኮ ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ ጎል አጥብቃ በምትፈልገበት ጨዋታ ሉዊስ ቻቬዝ ከ28 ሜትር ርቀት ያስቆጠራት የቅጣት ምት ከምርጦቹ ተርታ ተሰልፋለች።
7 ኪሊያን ምባፔ - ፖላንድ
በኳታር የአለም ዋንጫ ስምንት ጎሎችን አስቆጥሮ የወርቅ ጫማ የተሸለመው ፈረንሳዊው ኪሊያን ምባፔ ፖላንድን በጥሎ ማለፉ ሲያሰናብቱ በ74ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎል በአለም ዋንጫው ከታዩ ድንቅ ጎሎች አንዷ ናት ብሎ ፊፋ ይፋ አድርጓል።
8 ሪቻርልሰን - ደቡብ ኮሪያ
ብራዚል በጥሎ ማለፉ ደቡብ ኮሪያን 4 ለ 1 ስትረታ ሪቻርልሰን ሶስተኛዋን ጎል አስቆጥሯል። ሪቻርልሰን በሚገርም ብቃት የተሻገረለትን ኳስ በጭንቅላቱ አብርዶ ለማርኪንሆስ አቀበለ፤ ማርኪንሆስ ደግሞ ለቲያጎ ሲልቫ ፤ ሲልቫ ለሪቻልሰን በአንድ ጊዜ ንክኪ ተቀባብለው ያስቆጠራት ማራኪ ጎል በእጩነት ቀርባለች። ሪቻርልሰን በሁለት ጎሎች ነው የሚፎካከረው።
9 ፓይክ ሲኡንግ ሆ - ብራዚል
በአለም ዋንጫው ያልተጠበቀ ጉዞ ያደረገችው ደቡብ ኮሪያ በጥሎ ማለፉ በብራዚል ስትሸነፍ ሴኡንግ ያስቆጠራት ብቸኛ ጎል ከአስሩ ድንቅ ጎሎች ውስጥ ተካታለች።
10 ኔይማር - ክሮሽያ
የክሮሽያውን ግብ ጠባቂ ዶሚኒች ሊቫኮቪችን አልፎ ጎል ማስቆጠር የአለም ዋንጫው ከባድ ፈተና ሆኖ ታይቷል። ብራዚልም አንድ ጎል ለማስቆጠር የመጀመሪያው ተጨማሪ ደቂቃ አጋማሽ ድረስ መጠበቅ ነበረባት። የኔይማር፣ ሮድሪጎ እና ሉካስ ፓኬታ ድንቅ መጣመር የታየባት ጎል የአለም ዋንጫው ምርጥ ጎል ክብርን ለመቀዳጀት ከእቹዎቹ ውስጥ ተካታለች።