ለእግር ኳስ ፈርጡ ሜሲ ትልቅ ትርጉም ያለው የአለም ዋንጫ ፍጻሜ ዛሬ ይደረጋል
90 ሺህ ተመልካቾች በሚታደሙበት የሉሳይል ስታዲየም አርጀንቲና ሶስተኛውን የአለም ዋንጫ ለማንሳት ከፈረንሳይ ትፋለማለች
ከዋንጫ ፍልሚያው አስቀድሞ በስታዲየም የሚደረገው የኳታሩ የአለም ዋንጫ ደማቅ የመዝጊያ ስነስርአትም ይጠበቃል
ኳታር ቢሊየን ዶላሮችን አውጥታ በደማቅ ሁኔታ ያስተናገደችው 22ኛው የአለም ዋንጫ ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል።
የ1978ቱን የአለም ዋንጫ አዘጋጅታ ያነሳችው የሊዮኔል ሜሲ ሀገር ከ36 አመት በኋላ ሶስተኛውን የአለም ዋንጫ ወደ ቦነስ አይረስ ለመውሰድ ከ2018ቷ ሻምፒዮን ፈረንሳይ ጋር ትፋለማለች።
የሰባት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ሊዮኔል ሜሲ ከሀገሩ ጋር ትልቁን ድል ለመቀዳጀት ይጫወታል።
ሜሲ በ2014ቱ የብራዚል የአለም ዋንጫ ውሃ ሰማያዊ እና ነጭ ለባሾቹን ለፍጻሜ ቢያደርስም፥ በማሪዮ ጎትዘ ብቸኛ ጎል በጀርመን ዋንጫውን መነጠቃቸው ይታወሳል።
የፓሪስ ሴንት ጄርሜን ኮከቡ በኳታር ከቡድን አጋሮቹ ጋር ያለው መግባባት ግን ዛሬ ለፈረንሳይ በቀላሉ እጅ እንዳይሰጡ ያግዛቸዋል ነው የተባለው።
በኳታር ከኪሊያን ምባፔ እኩል አምስት ጎሎችን ያስቆጠረው ሜሲ የወርቅ ጫማውን ለመውሰድም ይፎካከራል።
በ1998ቱ የአለም ዋንጫ ከሰማያዊዮቹ ጋር ዋንጫ ያነሱት ዲዲየር ዴሻምፕ ደግሞ ፈረንሳይን በአሰልጣኝነት እየመሩ በሩስያ ያሳኩትን በኳታር ለመድገም የሉሳይል ስታዲየሙን ትንቅንቅ ይጠብቃሉ።
አርጀንቲና እና ፈረንሳይ በአለም ዋንጫው ሶስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን በሁለቱ አርጀንቲና አሸንፋለች።
በአለም ዋንጫ ለፍጻሜ በመድረስም አርጀንቲና (6) በፈረንሳይ (4) ላይ ብልጫ ትወስዳለች።
አርጀንቲና በዛሬው የሉሳይል ስታዲየም ፍልሚያ ድል የምታደርግ ከሆነ በመክፈቻ ጨዋታ ተሸንፋ (በሳኡዲ አረቢያ) ዋንጫ በማንሳት የስፔንን ታሪክ ትጋራለች።
ፈረንሳይ ድል ካደረገች የአለም ዋንጫን በተከታታይ በማንሳት ሶስተኛዋ ሀገር ትሆናለች። ጣሊያን የ1934 እና የ1938ቱን ፤ ብራዚል የ1958 እና የ1962ቱን ዋንጫ ማንሳታቸው ይታወሳል።
ባልተጠበቁ ክስተቶች ተሞልቶ ለስፖርት አፍቃሪዎች ሁነኛ የመዝናኛ ምንጭ ሆኖ የሰነበተው የኳታር የአለም ዋንጫ ከ5 ቢሊየን በላይ ሰዎች ተመልክተውታል።
ከተጠባቂው የፍጻሜ ፍልሚያ በፊት የሚደረገውን ደማቅ የመዝጊያ ስነስርአትም ከ90 በላይ ተመልካቾች በሉሳይስል ስታዲየም ቢሊየኖች ደግሞ በቴሌቪዥን መስኮት ይከታተሉታል።